ቀጥታ፡

ለሁለተኛ ጊዜ በዩኒቨርሲቲዎች ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በጋምቤላ ክልል ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል

ጋምቤላ ፤ ሐምሌ 15/ 2015(ኢዜአ)፡- ለሁለተኛ ጊዜ  በዩኒቨርሲቲዎች  ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ  ፈተና በጋምቤላ ክልል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ የፈተና ሂደት ክትትል ግብረ ኃይል አስታወቀ። 

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ ዘንድሮ የሚፈተኑ ከ11 ሺህ በላይ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን እንደሚያስተናግድ ገልጿል።

የግብረ ኃይሉ ጸሐፊና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሴ ጋጄት፤ ባለፈው ዓመት የነበሩትን ተሞክሮዎች መሰረት በማድረግ ለዘንደሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ብሄራዊ ፈተና አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

ባለፈው ዓመት የመጀመሪያ ጊዜ እንደመሆኑ የተለያዩ ክፍተቶች እንደነበሩ አስታውሰው፤ በዘንድሮው ዓመት የነበሩ ክፍተቶችን በሚያስተካከል  መልኩ ቅድመ መሰናዶ መደረጉን ተናግረዋል።

በክልሉ ሁሉም አስፈታኝ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን በስነ- ልቦናና በክህሎት የመገንባትና የማብቃት ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ ሰሞኑን ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር በአንፃራዊነት እየተረጋጋ በመምጣቱና በፈተናው ሂደቱ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ እንዳማይኖር በክልሉ መንግስት ታምኖበት ፈተናውን ስኬታማ በሆኑ መልኩ ለመስጠት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በፈተናው ወቅትም አስፈላጊውን ጥበቃና ክትትል የሚያደርግ በቂ የጸጥታ ኃይል መመደቡን የገለጹት አቶ ሙሴ ፤ ወላጆች ያለምን ስጋት ልጆቻቸው ወደ ፈተና ማዕከሉ እንዲልኩም ጥሪ አቅርበዋል።

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡጁሉ ኡኮክ በበኩላቸው ተቋሙ ዘንድሮ  የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ከ11 ሺህ በላይ የማህበራዊና የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስፈተን መዘጋጀቱን ገልጸዋል። 

ተማሪዎች በግቢው በሚኖራቸው ቆይታ አስፈላጊው የመጠለያ፣ የምግብ፣ የህክምናና ሌሎች መሰረታዊ ማህበራዊ አገልግሎቶች የተመቻቸላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው ነገ የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኝ ተማሪዎችን መቀበል እንደሚጀምር ዶክተር ኡጁሉ አስታውቀዋል። 

በሀገር አቀፍ ደረጃ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሄራዊ ፈተና ከሐምሌ 19 ቀን 2015 ዓ.ም  ጀምሮ እንደሚሰጥ ቀደም ብሎ መገለጹ ይታወሳል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም