ተመራቂ ተማሪዎች ለሕዝብ ጥቅምና አገራዊ ለውጥ በቅንነትና በታማኝነት ሊሰሩ ይገባል - ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ - ኢዜአ አማርኛ
ተመራቂ ተማሪዎች ለሕዝብ ጥቅምና አገራዊ ለውጥ በቅንነትና በታማኝነት ሊሰሩ ይገባል - ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 15/2015 (ኢዜአ) ፡- ተመራቂ ተማሪዎች ለሕዝብ ጥቅምና አገራዊ ለውጥ በቅንነትና በታማኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ተናገሩ።
ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በሁለተኛ ዲግሪ፣ በመጀመሪያ ዲግሪና በዲፕሎማ መርሃ-ግብር ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 550 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታችሁ ያካበታችሁትን እውቀት ለአገር ለውጥ ማዋል አለባችሁ።
''ዛሬ የተመረቃችሁ ተማሪዎች የለበሳችሁት የመመረቂያ ጋዎን የደስታ ብቻ ሳይሆን ትልቅ ህዝባዊ አደራን የምትቀበሉበትና ህዝብን የምታገለግሉበት አደራም ጭምር ነው" ብለዋል።
ተመራቂዎች የተሻለ አማራጮችን በመፈተሽ ሥራ ጠባቂ ሳይሆን ሥራ ፈጣሪ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
ዛሬ ያገኛችሁት ዲግሪ ብቻውን ግብ ሊሆን አይገባም ያሉት ሚኒስትሯ ሁልጊዜም ራሳችሁን ለማሻሻል መሥራት ይገባችኋል ብለዋል።
የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ባለፉት 70 ዓመታት የተማረ የሰው ሃይል በማፍራት በኢትዮጵያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ይሄን ተግባሩን አጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ተመራቂዎችም ችግር ፈቺ ሥራዎችን በማከናወን የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
ዩኒቨርሲቲው አገሪቱ የምትፈልገውን የሰው ኃይል ለማፍራት የሥርዓተ ትምህርት ማሻሻያ ማድረጉን ጠቁመው በማሻሻያው መሰረት ተማሪዎችን ተቀብሎ እያሰለጠነ መሆኑን ገልጸዋል።
"ተመራቂ ተማሪዎች በአገሪቱ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሄ ማፈላለግ ላይ የድርሻችሁን ልትወጡ ይገባል" ሲሉም አሳስበዋል።
በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ተመራቂዎች የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።