ቀጥታ፡

ሌብነትን የሚጸየፍና ሥነ-ምግባር ያለው ሲቪል ሰርቫንት እንዲገነባ ምሩቃን የበኩላቸውን ሚና መወጣት አለባቸው - ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ

አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 15/2015 (ኢዜአ) ፦ የሕዝብ አገልጋይነትንና አመለካከትን በጽናት በመያዝ ሌብነትን የሚጸየፍና ሥነ-ምግባር ያለው ሲቪል ሰርቫንት እንዲገነባ ምሩቃን የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ጥሪ አቀረቡ።

የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ በተለያዩ መርኃ ግብሮች በቀንና በማታ ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 377 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል። 


 

ከተመረቁት ተማሪዎች መካከል 180ዎቹ በመጀመሪያ ዲግሪ፣ 2 ሺህ 186ቱ በሁለተኛ ዲግሪ እና 11ዱ ደግሞ በሦስተኛ ዲግሪ የተመረቁ መሆናቸው ተገልጿል።   

ከተመራቂዎቹ መካከል 23 በመቶው ሴቶች 77 በመቶው ደግሞ ወንዶች መሆናቸው ተጠቁሟል። 

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ፐብሊክ ሰርቪሱ በአገልግሎት አሰጣጥ ጅምር ለውጦችን እያመጣ ነው። 

ለዚህም የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፐብሊክ ሰርቪሱ ያሉበትን ጉድለቶች በመቅረፍና አገልግሎቱን በማሻሻል አብርክቶው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።  

ይሁንና አሁንም ፐብሊክ ሰርቫንቱ አገልጋይነትን በመላበስ በኩል ብዙ መሥራት አለበት ነው ያሉት። 

በመሆኑም የሕዝብ አገልጋይነት አመለካከትን በጽናት በመያዝ ሌብነትን የሚጸየፍና ሥነ-ምግባር ያለው ሲቪል ሰርቫንት እንዲገነባ ምሩቃን የበኩላቸውን ሚና መወጣት አለባቸው ብለዋል። 

ምሩቃን በተለይም የአገራዊ ምክክር መድረክ እንዲሳካ እንዲሁም በተሰማሩበት የሥራ መስክ ለአገሪቱ እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል።

ዩኒቨርሲቲው ለድኅረ ምረቃ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን ለሚያደርገው ጥረት ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ ዶክተር ሳሙኤል አረጋግጠዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ላለፉት 28 ዓመታት የሰው ኃይል በማልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።


 

ከዚህም በተጨማሪ በመንግሥት የተዘረጉ ሪፎርሞች ትግበራን በማማከር ዩኒቨርሲቲው ለአገር እድገትና ብልጽግና የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑንም ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ተወዳዳሪና ተመራጭ የድኅረ ምረቃና የምርምር ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ነው ፕሬዝዳንቱ ያብራሩት።

የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት 28 ዓመታት ከ65 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ያስመረቀ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 600 የሚሆኑት የጐረቤት አገራት የመንግሥት ሠራተኞች መሆናቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም