የአረንጓዴ አሻራ ልማት እንዲሳካ የበኩሌን ጥረት እያደረኩ ነው-የፌዴራል ፖሊስ አባል ዋና ሳጅን ኤርሚያስ ተካ - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ ልማት እንዲሳካ የበኩሌን ጥረት እያደረኩ ነው-የፌዴራል ፖሊስ አባል ዋና ሳጅን ኤርሚያስ ተካ
ሐረር፤ ሐምሌ 15 /2015 (ኢዜአ) ፡- የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር እንዲሳካ የበኩሌን ጥረት እያደረኩ ነው ሲሉ የፌዴራል ፖሊስ አባል ዋና ሳጅን ኤርሚያስ ተካ ገለጹ።
ዋና ሳጅን ኤርሚያስ ተካ ትውልድና እድገታቸው ሐረር ከተማ ቀበሌ 13 በተለምዶ ሞቢል ድልድይ አካባቢ ነው።
ቤተሰቦቻቸው በ1997 ዓ.ም የጀመሩትን የአረንጓዴ ልማት ስራም በማጠናከር የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞችን በማፍላት ለገበያ እያቀረቡ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የዘረጉት የአረንጓዴ አሻራ ልማት ላይ ተሳትፏቸውን በማጎልበትና ችግኞችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበረሰቡ በማዳረስ ልማቱ ስኬታማ እንዲሆን የበኩላቸውን እየተወጡ ነው።
አሁን ላይ ቡና፣ አቦካዶ፣ የግቢ አበቦች፣ አትክልት እንዲሁም "እንደ ኪኒን ዛፍ" ፣ጽድ፣ወይራ፣ነጭ ባህርዛፍን ጨምሮ ሌሎች የደንና ለምግብነት የሚያገለግሉ 25 ሺህ ችግኞችን ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
"አንዳንድ ሰው ቦታ ተሰጥቶት ገንዘብ ይጠብቃል፤ እኔ ግን የዛሬ አምስት ዓመት የቤተሰቦቼን የአረንጓዴ ልማት ስራን ለማስቀጠል የአትክልትና ሌሎች ችግኞችን ከአዲስ አበባ በ5 ሺህ ብር ገዝቼ አስፋፋው፤ በአሁኑ ወቅት አንድ ችግኝ በ10 ብር ብሸጥ 250 ሺህ ብር ማግኘት እችላለሁ" ይላሉ ዋና ሳጅን ኤርሚያስ ።
ለሁሉም ነገር መንግስትን መጠበቅ የለብንም፤ ሐረር ውስጥ ውሃ የለም ይባላል መሬት ውስጥ ብንቆፍር በቀላሉ ውሃ ማግኘት እንችላለን፤ እኔም መጀመሪያ ሰርቼ ማሳየት ነው የምፈልገው ብዬ ሁለት ጉድጓድ በመቆፈር ለአትክልቶቼና ለሌሎች አገልግሎት እየተጠቀምኩ እገኛለው ብለዋል።
በሚያባዟቸውና በሚያጸድቋቸው እጽዋቶች ተረፈ ምርት መኖ በማዘጋጀት እንስሳትን በማርባት ከዘርፉ እየተጠቀሙ መሆናቸውን የገለጹት ዋና ሳጅን ኤርሚያስ ፤ በተለይ ደግሞ በሐረሪ ክልል ቀደምት የነበሩና የጠፉ ፍራፍሬ ተክሎችን የመመለስ ስራም እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በረሃማነትን በልምላሜ ለመተካት የዘረጉት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እንዲሳካ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ዋና ሳጅን ኤርሚያስ አስረድተዋል።
የአረንጓዴ አሻራና ተዛማጅ የግብርና ስራዎች አረንጓዴ ልማትን እንዲስፋፋ ከማድረጉ ባለፈ ለእሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው የገቢ ምንጭ በመሆን ኑሯቸውን እንዲደግፋ ስላስቻላቸው በአረንጓዴ ልማት ስራዎች በመሳተፋቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ዋና ሳጅን ኤርሚያስ በከተማ ውስጥ በጠባብ ቦታ ላይ እንዴት ሁሉንም የግብርና ስራዎችን መስራት እንደሚያስችል ለሌሎች ያስተማሩ ናቸው ያሉት ደግሞ የሐረሪ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሻሚ አብዲ ናቸው።
በተለይ የቡና ችግኞችን ለቢሮው በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር እያገዘ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሞዴል በመሆናቸው ቢሮው አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ እያበረታታናቸው ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሐምሌ 10 ቀን 2015ዓ.ም ባስተላለፉት መልዕክት፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ኢትዮጵያን የመጠበቅ፣ የማክበርና የማበልጸግ ፣ ታሪክ የመቀየርና ለትውልድ የመትረፍ ጉዳይ ነው።