የደቡብ ሱዳን ፓርላማ የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የማጽደቅ ሂደት እንዲያፋጥን ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ሱዳን ፓርላማ የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የማጽደቅ ሂደት እንዲያፋጥን ተጠየቀ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/2015(ኢዜአ) :-የደቡብ ሱዳን ፓርላማ የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት(CFA) የማጽደቅ ሂደት እንዲያፋጥን ጥሪ ቀረበ።
የናይል የውሃ ሀብቶች አጠቃቀም እና የትብብር ማዕቀፍ(Cooperative Framework Agreement) ስምምነቱን የተመለከተ አውደ ጥናት በጁባ ተካሄዷል።
በውይይቱ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር አምባሳደር ፍስሐ ሻወል፣ በደቡብ ሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲ፣የናይል ተፋሰስ አገራት ተወካዮችና የደቡብ ሱዳን ሕግ አውጪ ምክር ቤት የብሔራዊ የሽግግር ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተገኝተዋል።
አምባሳደር ፍስሐ ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር የተለየ ቦታ እንደምትሰጠው እና በቀጣናው ካሉ ጠንካራ አጋሮች መካከል እንደ አንዷ እንደምታያት ገልጸዋል።
የደቡብ ሱዳን መንግስት የፓርቲ ጉዳዮች ዋና ተጠሪ ሬቤካ ጆሹዋ ኦካቺ “ናይል ከፈጣሪ ለሁላችንም የተሰጠ ስጦታ ነው፤ ሁሉም ከናይል ወንዝ ተጠቃሚ መሆን አለበት” ብለዋል።
የደቡብ ሱዳን ፓርላማ የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን የማጽደቅ ሂደት እንዲያፋጥንም አሳስበዋል።
የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት እ.አ.አ 2006 የተዘጋጀ ሲሆን የናይል ተፋሰስ አገራት የውሃ ሀብቶችን በትብብር ማልማት እና ማስተዳደር የሚቻልባቸው ሁኔታዎች ያስቀመጠ ነው።