ቀጥታ፡

አርሲ ዩኒቨርስቲ ለአትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና ለሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጠ

አዳማ ሐምሌ 15/2015(ኢዜአ)፦ አርሲ ዩኒቨርሲቲ ለአትሌት ቀነኒሳ በቀለ እና ለኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷል።

ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።


 

አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የኢትዮጵያ ስም በዓለም አደባባይ በማስጠራቱ እንዲሁም ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት እየሰሩ በመሆናቸው የክብር ዶክትሬት ዲግሪው መሰጠቱን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዱጉማ አዱኛ ገልጸዋል።

ዶክተር ዱጉማ በንግግራቸው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የሀገራችን ባንዲራ በዓለም አደባባይ እንዲውለበለብ በማድረግ ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ያስጠራ ጀግና ነው ብለዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ በጎ ገፅታና ጀግንነት በዓለም አደባባይ እንዲተዋወቅና እንዲጠራ በማድረግ ታላቅ ገድል የፈፀመ በመሆኑ የክብር ዶክትሬት ዲግሪው እንደተሰጠው ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዘዳንት ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ በሀገራችን ሰላም፣ መቻቻልና አብሮነት እንዲጎለብት ሀላፊነታቸውን እየተወጡ ያሉ አባት በመሆናቸው የክብር ዶክትሬቱ ተሰጥቷቸዋል ብለዋል ዶክተር ዱጉማ።

የሃይማኖት መቻቻልና አንድነት እንዲጎለብት በማድረግ በኩል በሀገራዊ ገፅታ ግንባታ የድርሻቸውን በመወጣታቸው የክብር ዶክትሬት ዲግሪው እንደተሰጣቸውም ነው ፕሬዚደንቱ ያመላከቱት።

የአርሲ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የሙያ መስኮች በስድስት ኮሌጆች ያሰለጠናቸውን 621 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።


 

አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የክብር ዶክትሬት ዲግሪውን በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ አማካኝነት ተቀብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም