የኢትዮጵያ አየር መንገድ አለም አቀፍ ክስተቶችን ተቋቁሞ ትርፋማ እንዲሆን የሰራተኛው ሚና ከፍተኛ ነው-አቶ መስፍን ጣሰው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አለም አቀፍ ክስተቶችን ተቋቁሞ ትርፋማ እንዲሆን የሰራተኛው ሚና ከፍተኛ ነው-አቶ መስፍን ጣሰው
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 15/2015(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ አለም አቀፍ ክስተቶችን ተቋቁሞ ትርፋማ ሆኖ እንዲቀጥል የሰራተኞች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚው መስፍን ጣሰው ተናገሩ።
ዋና ስራ አስፈጻሚው ይህን ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ተቀዳሚ መሰረታዊ የሰራተኞች ማህበር የተመሰረተበት 60ኛ አመት ክብረ በዓል ላይ ነው።
አየር መንገዱ በአፍሪካ እንዲሁም በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ተጽዕኖ ፈጣሪ አየር መንገድ ሆኖ እንዲቀጥል ሰራተኞች ጉልህ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።
በተለይም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት በአለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ የአየር መንገዶች ላይ ያሳደረው ጫና ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰው አየር መንገዱ ተጽዕኖውን በመቋቋም ትርፋማ ሆኖ እንዲቀጥል ሰራተኞች ችግሩን ተጋፍጠው ማሳለፋቸውን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ተቀዳሚ መሰረታዊ የሰራተኞች ማህበር ሚናም ከፍተኛ እንደነበርም ጨምረው ገልጸዋል።
ማህበሩ የኢንዱስትሪ ሰላምን ለማስጠበቅ፣ የሰራተኞችን መብትና ጥቅም ለማስከበር ከአየር መንገዱ ግሩፑ የማናጅመንት አባላት ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የአየር መንገዱን በአለም አቀፋ ደረጃ ያለውን ተወዳዳሪነት ለማስቀጠል የሰራተኞችን ጥቅም በማስጠበቅና ምቹ የስራ ከባቢን በማስጠበቅ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
አየር መንገዱ የሰራተኞችን ጥቅም ለማስከበር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸው ለ5 ሺህ ሰራተኞች የሚሆን ቤት ለመገንባት ቦታ መረከቡን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ተቀዳሚ መሰረታዊ የሰራተኞች ማህበር ፕሬዝዳንት ኪያ ለማ በበኩላቸው ማህበሩ የሰራተኞችን መብትና ጥቅም ለማስከበር፣ ሰላማዊ የስራ አካባቢን ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የሰራተኞችን ጥቅም ለማስጠበቅ ከተለያዩ ባንኮች ጋር ትስስር በመፍጠር የቤትና መኪና ብድር የሚያገኙበትን መንገድ እያመቻቸ እንደሚገኝ ፕሬዝዳንቷ ተናግረዋል።
ማህበሩ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ክስተቶች ምክንያት ችግር ውስጥ የወደቁ አካባቢዎችን በመደገፍ ማህበራዊ ሀላፊነቱን እየወጣ እንደሚገኝም ጨምረው ገልጸዋል።