ቀጥታ፡

የዓለም አገራት በሽታዎች ወረርሽኝ ሳይሆኑ በፊት ቅድመ መከላከል ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል-አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/2015(ኢዜአ):- የዓለም አገራት በሽታዎች ወረርሽኝ ሳይሆኑ በፊት አስቀድሞ መከላከል ላይ ትኩረት አድርገው መስራት እንደሚገባቸው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጄኔቫ ቢሮ እና በስዊዘርላንድ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው ገለጹ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የወረርሽኝ ቅድመ መከላከልና ምላሽ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን የተቋቋመው የበይነ መንግስታት ጥምረት እና ዓለም አቀፍ የጤና ሕጎች ማሻሻያ እንዲደረግባቸው የሚሰራው የባለሙያዎች ቡድን የመጀመሪያ የጋራ ስብሰባቸውን በጄኔቫ አድርገዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጄኔቫ ቢሮ እና በስዊዘርላንድ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው በሽታዎች ሳይዛመቱ በፊት መቆጣጠር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም የዓለም አገራት በሽታዎች ወደ ወረርሽኝ ከመቀየራቸው በፊት አስቀድሞ መከላከል ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በዓለም የጤና ሕጎች ላይ ያሉ የፍትሐዊነት እና እኩልነት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ አስገዳጅ ማሻሻያዎች መደረግ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በጤና ጉዳዮች ላይ የሚሰራው የአፍሪካ ቡድን አስተባባሪ ናት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም