በእንጦጦ ፓርክ አካባቢ እየተንቀሳቀሱ ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በእንጦጦ ፓርክ አካባቢ እየተንቀሳቀሱ ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2015(ኢዜአ):-በአዲስ አበባ ከተማ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው እንጦጦ ፓርክ መግቢያ አካባቢ እየተንቀሳቀሱ ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ ሦስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፓሊስ አስታወቀ።
ግለሰቦቹ የአካባቢውን ጭር ማለትና የፖሊስ አባላትን እግር ጠብቀው ወንጀል ሲፈፅሙ መቆየታቸውን የምርመራ መዝገባቸው እንደሚያስረዳ ፓሊስ ገልጿል።
ወንጀል ፈፃሚዎቹ በፓርኩ ውስጥ በመዝናናት ላይ የነበሩ ሴት ተማሪዎችን በሽጉጥ በማስፈራራት ደብተሮችና አጀንዳ ያለበትን ቦርሣ ቀምተው ሲያመልጡ ተማሪዎቹ ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ ከሱሉልታ በሚመጣ የትራንስፖርት ታክሲ ገብተው ለማምለጥ ሲሞክሩ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ነው ያመለከተው፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ከተያዙ በኋላ በተከናወነ ምርመራ የማስፋት ስራ አንድ ህገ ወጥ ሽጉጥ ከመሰል አስራ አምስት ጥይት ጋር፣ 50 ፓውንድ፣ የዛምቢያ ባለ ሁለት መቶ የገንዘብ ኖት፣ የተለያየ የዋጋ ግምት ያላቸው ሞባይል ስልኮች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
በፓርኩ ዙሪያና ውስጥ በቂ የፖሊስ ኃይል መደበኛ ስራውን እያከናወነ ስለሆነ ሕብረተሰቡ መደበኛ እንቅስቃሴውን ያለ ስጋት ማከናወን እንደሚችል ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡