የጣሊያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ባለው ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ የመሰማራት ፍላጎት አላቸው - ላቲዛ ፒዚ - ኢዜአ አማርኛ
የጣሊያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ባለው ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ የመሰማራት ፍላጎት አላቸው - ላቲዛ ፒዚ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ14 /2015(ኢዜአ)፡- የጣሊያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ባለው ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው በአፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ የጣሊያን ኢንተርፕራይዞች ልማት ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ላቲዛ ፒዚ ተናገሩ።
ማኅበሩ በጣሊያን የሚገኙ ዋና ዋና ኢንዱስትሪዎችን ባንኮችንና መካከለኛና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በአባልነት የያዘ ሲሆን፤ በዋናነት አፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ ላይ ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ይሰራል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋን ጨምሮ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ከማኅበሩ ዋና ዳይሬክተር ላቲዛ ፒዛ ጋር በጣሊያን ርዕሰ መዲና ሮም ተወያይተዋል።
ውይይታቸውም በዋናነት በኢትዮጵያ ባሉ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ የጣሊያን ኩባንያዎች ኢንቨስት በሚያደርጉበት ጉዳይ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግሥት ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆኑ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ማድረጉን ተናግረዋል።
በተለይም በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዕቀፍ ውስጥ የተደረጉ የሕግ ማሻሻያዎችን ለአብነት የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ ማሻሻያዎቹ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ምቹ ሁኔታ የፈጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
መንግሥት በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን ቱሪዝምና አይ ሲቲ ዘርፎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመሆኑም የጣልያን ኩባንያዎች በተለይ በግብርና ማቀነባበር፣ ማዕድን፣ ኮንስትራክሽንና ታዳሽ ኃይል ዘርፍ ቢሰማሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ ኢንቨስትመንትና ንግድን ለማሳለጥ ምቹ መሆናቸውን ሚኒስትሯ አብራርተዋል።
የጣሊያን ኢንተርፕራይዝ የአፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ ልማት ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ላቲዛ ፒዚ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ጣሊያን ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው አገራት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ እየወሰዳቸው ያሉ የማሻሻያ እርምጃዎችንም አድንቀዋል።
ይህም የጣሊያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር ስለመሆኑም አውስተዋል።
ኢትዮጵያ ለጣሊያን ኩባንያዎች ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን ጠቁመው አሁን ላይ በርካታ የጣሊያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ለመሰማራት ፍላጎት እያሳዩ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል።
ከዚህ አኳያ ማኅበሩ የጣሊያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ በቀጣይነት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
ማኅበሩ የጣሊያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ በአካል ተገኝተው እንዲመለከቱ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ጨምረው ገልጸዋል።