ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መንግስት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን ተጨባጭ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2015(ኢዜአ)፦  የኢትዮጵያ መንግስት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን ተጨባጭ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።


 

መንግስት መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ ዲፕሎማቶች እና የዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ ተቋማት ኃላፊዎች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጠ።

ማብራሪያውን የሰጡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እና የፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ናቸው።


 

አቶ ደመቀ የኢትዮጵያ መንግስት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሙሉ ለሙሉ እንዲተገበር ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው ስምምነቱን ለመፈጸም ተጨባጭ የሚባሉ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸዋል።

እስካሁን ያለው የስምምነቱ አፈጸጻም ስኬታማ የሚባል ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል የሽግግር ፍትሕ ሂደት አማራጮችን አስመልክቶ በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄዱ ውይይቶች በርካታ የሕብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

የሽግግር ፍትሕ እውነትን በመናገር፣ቁስልን በማከም እና እርቅን በማምጣት የሰላም ሂደቱን ይበልጥ እንደሚያጸና ጠቅሰው ሂደቱ ፍትሕ በማስፈንና ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ያሉ ተጎጂዎች እንዲካሱ የሚያደርግ መሆኑን ነው አቶ ደመቀ ያብራሩት።


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ማብራሪያውን አስመልክቶ ለአገር ውስጥ እና ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ የሽግግር ፍትሕ ሂደት አማራጭ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ለማጽናት ቁልፍ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም