የቁልቢ ገብርኤል ክብረ-በዓል በሰላም እንዲከበር በቂ ዝግጅት ተደርጓል-የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል - ኢዜአ አማርኛ
የቁልቢ ገብርኤል ክብረ-በዓል በሰላም እንዲከበር በቂ ዝግጅት ተደርጓል-የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2015(ኢዜአ)፦ የቁልቢ ገብርኤል ክብረ-በዓል በሰላም እንዲከበር የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገልጿል።
የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ሐምሌ 19 ቀን 2015 ዓ.ም የሚከበረው የቁልቢ ገብርኤል ክብረ-በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ የመከላከያ ሠራዊት፤ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ፖሊስ፣ የድሬዳዋ ፖሊስና የሀረሪ ፖሊስ ከአካባቢው አስተዳደር አካላት፣ ከሃይማኖት አባቶች እና ከአካባቢው ማኅብረተሰብ ጋር በመቀናጀት ተጋላጭና ልዩ ትኩረት የሚፈልጉ አካባቢዎችን በመለየት ሕዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን በሰላም እንዲያከብር በቂ ዝግጅት አድርጎ ወደ ተግባር መግባቱን ገልጿል።
የጋራ ግብረ-ኃይሉ አክሎም በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ እና በምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች ሰላምና ደህንነት እያስከበረ መቆየቱንና አሁን ላይ የአካባቢው ሰላም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።
የጋራ ግብረ ኃይሉ በተመሳሳይ የፀጥታውን ሁኔታ የበለጠ ለማጠናከር በሁሉም አቅጣጫ አስፈላጊውን ጥበቃና ክትትል በማድረግ ላይ እንደሚገኝም አመላክቷል፡፡
በበዓሉ ላይ ለሚታደሙ ሕዝበ ክርስቲያን የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አሸከርካሪዎች የትራፊክ ሕግን አክብረው በማሽከርከር የበዓሉ ታዳሚዎች ያለ ምንም የትራፊክ አደጋ በዓሉን በሰላም አክብረው እንዲመለሱ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በመውሰድ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የጋራ ግብረ-ኃይሉ አሳስቧል።
የአካባቢው ኅብረተሰብ ለእንግዶቹ ቅድሚያ በመስጠት የቆየ የእንግዳ ተቀባይነት ባህሉ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።
በተጨማሪም ለሰላምና ደኅንነት ስጋት የሆኑ ነገሮችን ሲመለከት በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች ጥቆማ በመስጠት የድርሻቸውን እንዲወጡ የጋራ ግብረ-ኃይሉ ጥሪ ማቅረቡን የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል።