ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የብስክሌት ስፖርትን ለማስፋት የተከናወኑ ተግባራት ውጤት አስገኝተዋል--የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2015(ኢዜአ):- በኢትዮጵያ የብስክሌት ስፖርትን ለማስፋት የተከናወኑ ተግባራት ውጤት ማስገኘታቸውን የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ገለጸ።

በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከተካተቱ የስፖርት አይነቶች መካከል የብስክሌት ስፖርት አንዱ ነው።

ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ጨዋታ መሳተፍ ከጀመረችበት እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር ከ1956 የሜልቦርን ኦሊምፒክ ጀምሮ በብስክሌት ስፖርት በተለያየ ጊዜ ተሳትፎ አድርጋለች።

ያም ሆኖ እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር ከ1992 የባርሴሎና የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በኋላ በነበሩ ስድስት ተከታታይ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ ከብስክሌት ስፖርት ውድድር ርቃ ቆይታለች።

ባለፉት ሁለት ተከታታይ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዳግም ወደ ተሳትፎ መመለስ ችላለች።

የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን የኦሊምፒክ ተሳትፎን ለማስቀጠልና ስፖርቱን በአገር አቀፍ ደረጃ ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ዛሬ በሰጠው መግለጫ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ወንድሙ ኃይሌ ፌዴሬሽኑ በተያዘው ዓመት ስኬታማ ሥራዎች ማከናወኑን ተናግረዋል።

አራት ብስክሌተኞች ወደ ፕሮፌሽናል ደረጃ በማሳደግ የውጭ ክለቦችን እንዲቀላቀሉ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብስክሌተኞች በዓመቱ በተለያዩ አገራት በተካሄዱ ሻምፒዮናዎች ላይ አመርቂ ውጤት ማስመዝገባቸውን ጠቁመዋል።

ለአብነትም በዓመቱ በጋና በተደረገ የአፍሪካ ብስክሌት ውድድር አንድ ወርቅና ሁለት ነሐስ ሜዳሊያ በመሰብሰብ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች ብለዋል።

ፌዴሬሽኑ በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት 2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ በብስክሌት ስፖርት ለመሳተፍ፤ በተለያዩ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች በምታስመዘግበው ድምር ውጤት በመሆኑ ውድድሮች ላይ እየተሳተፈች መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ ነሐሴ ወር ላይ በስኮትላንድ በሚካሄደው የዓለም ብስክሌት ሻምፒዮና ላይ እንደምትሳተፍ ጠቁመዋል።

የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ሰለሞን በቀለ ስፖርቱ ትኩረት ባይሰጠውም ፌዴሬሽኑ አገርን በተለያዩ መድረኮች እየወከሉ የሚወዳደሩ ውጤታማ ስፖርተኞች እያፈራ ነው።

ፌዴሬሽኑ በተለያዩ ውድድሮች ከመሳተፍ በተጨማሪ የአፍሪካ ውድድሮችን በኢትዮጵያ በማዘጋጀት ስፖርቱን ለማሳደግና የአገሪቱን ገጽታ ለመገንባት ጭምር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በ2016 ዓ.ም የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮናን በኢትዮጵያ ለማዘጋጀት ፌዴሬሽኑ ጥያቄ እንዳቀረበና በአፍሪካ ብስክሌት ማኅበር በኩል አወንታዊ ምላሽ እንዳለም በመግለጫው ተነስቷል።

ፌዴሬሽኑ ስፖርተኞች ሀገር ወክለው በዓለም አቀፍ ውድድር እንዲሳተፉ ለማድረግ የገንዘብ አቅም ውስንነት እየፈተነው መሆኑን ጠቀሶ ባለድርሻ አካላትን ድጋፍ እንደሚሻም በመግለጫው ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም