ቀጥታ፡

አገር አቀፍ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ በቀጣይ ሣምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2015(ኢዜአ):-አገር አቀፍ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ ሐምሌ 18 እና 19/2015 ዓ.ም  በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ገለጸ።   

የምክክር መድረኩን የንግድና ቀጣናዊ ትሥሥር ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በጋራ ማዘጋጀታቸው ተጠቁሟል።


 

የምክር ቤቱ ዋና ጸኃፊ ውቤ መንግሥቱ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መድረኩ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ትብብርና አጋርነት ለማጠናከር ወሳኝ ነው ብለዋል። 

በመድረኩ ላይ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት፣ ፖሊሲ አውጭዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የኃሳብ ልውውጥ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

በመድረኩ በአገሪቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱትን የግብርና፣ የቱሪዝምና ኢ-ኮሜርስ ዘርፎችን ለማነቃቃት የሚያስችሉ ውይይቶች ይደረጋሉ ነው ያሉት።  

የንግድ ሥርዓቱን የሚያውኩ ጉዳዮች እንዲፈቱ፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትንና ልማትን ለማስፋፋት የሚያስችሉ የመፍትሄ አቅጣጫ ለማፈላለግ እድል እንደሚሰጥም ጠቁመዋል። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም