ኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተውን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጎልበት እንደሚሰሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተውን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጎልበት እንደሚሰሩ ገለጹ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2015(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተውን የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ።
በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ በጃፓን ከሩዋንዳ አምባሳደር አርነስት ሩዋሚሲዮ ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ ያተኮረው በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።
አምባሳደር ዳባ የሁለቱ አገራት ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው እና ትብብራቸው በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለውን የለውጥ ስራዎችና የተገኙ ውጤቶችን የተመለከተ ማብራሪያ ለአምባሳደሩ ሰጥተዋል።
በጃፓን የሩዋንዳ አምባሳደር አርነስት ሩዋሚሲዮ በበኩላቸው በሁለቱ አገራት መካከል ያለው መልካም ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።
ሩዋንዳ ችግር ውስጥ በነበረችበት ወቅት ኢትዮጵያ የተጫወተችውን ሚና በማስታወስ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ሁለቱ ወገኖች በጃፓን በሚኖራቸው ቆይታ ለጋራ ጥቅም ከሌሎች የአፍሪካ አገራት አምባሳደሮች ጋር በቅንጅት ለመስራት መግባባት ላይ ደርሰዋል።
ኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1970ዎቹ ነው።
ሩዋንዳ በኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1978 እንዲሁም ኢትዮጵያ በኪጋሊ እ.አ.አ 2017 ኤምባሲያቸውን ከፍተው የዲፕሎማሲ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛሉ።
ሁለቱ አገራት እ.አ.አ በ2012 አጠቃላይ ትብብራቸውን ለማጠናከር፣ስትራቴጂካዊ ትብብር ለመፍጠር እና ቋሚ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ለማቋቋም የሚያስችላቸውን የጋራ መግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።