አምራች ኢንዱስትሪው ዘላቂ የሥራ እድል በመፍጠር እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ለማጠናከር እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት - ኢዜአ አማርኛ
አምራች ኢንዱስትሪው ዘላቂ የሥራ እድል በመፍጠር እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ለማጠናከር እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ14/2015(ኢዜአ):- የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ዘላቂ የሥራ እድል በመፍጠር ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ገለፀ።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልፈታህ የሱፍ ለኢዜአ እንደገለጹት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አዳዲስ የሥራ እድል በመፍጠርና በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ተሳትፎ በማድረግ ሰፊ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው።
ኢንተርፕራይዞቹ ምርታማነት እንዲጨምር ከማድረግ ባለፈ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በአገር ውስጥ ምርት እንዲተካ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአብነትም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ወደ ውጭ ከተላከ ምርት ከ37 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንም ገልጸዋል።
መካከለኛና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞቹ በየዓመቱ የሥራ አጥ ቁጥርን በመቀነስ፣ የአገሪቱን የኢኮኖሚና የምርት መጠን በማሳደግ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በአዲሱ የ2016 በጀት ዓመት በዘርፉ 200 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እየተሰራ ሲሆን ለእቅዱ ስኬታማነት የሁሉም ባለድርሻ አካላት አስተዋጽኦ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
በተለይም በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተፈጠረው አሰራርን በመጠቀም ኢንተርፕራይዞቹ የተሻለ ውጤት ሊያመጡ የሚችሉበትን መንገድ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።
የአማሔ ማኑፋክቸሪንግ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ አየለ በ2006 ዓ.ም በ2 ሚሊዮን ብር ካፒታልና በአንድ ሰው ሥራ በጀመሩት አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ፤ በ2015 ዓ.ም የ20 ሚሊዮን ብር ካፒታል መድረስ እንዳስቻላቸው ይናገራሉ።
ለዚህም በመንግሥት የተመቻቸላቸው የብድር አገልግሎትና የማሽኖች ግዥ ትልቅ ድጋፍ እንዳደረገላቸው ይናገራሉ።
በተለይ በኢትዮጵያ ታምርት የተፈጠረላቸው የገበያ ትስስር የሚያቀርቧቸው የኤሌክትሪክ ምጣድ፣ ምድጃና የኤሌክትሪክ ሽቦ ምርቶች ተፈላጊነት እንዲጨምር ማስቻሉን አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅትም በአጠቃላይ 70 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር የተቻለ ሲሆን የውጭ ምንዛሪና የመሥሪያ ቦታ ድጋፍ ካገኙ የተሻለ የሥራ እድል የመፍጠር እቅድ እንዳላቸው ገልፀዋል።
ከዝቅተኛ የልብስ ስፌት ሥራ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው የገቡት የልደት ጋርመንት ባለቤት አቶ ሲሳይ ዲቲ ደግሞ መንግሥት ባመቻቸው የቀረጥ ነፃና ሌሎች እድሎች በመጠቀም ሥራቸውን እንዳስፋፉ ይገልፃሉ።
በሁለት የልብስ ስፌትና የኦቨር ሉክ ማሽን በጥቂት መነሻ ካፒታል ሥራ እንደጀመሩ የሚናገሩት አቶ ሲሳይ አሁን ላይ ካፒታላቸው 10 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን ለ71 ሰው የሥራ እድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።
በዋናነት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተፈጠረው እድል ምርቶቹን ለማስተዋወቅ በመቻሉ የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶቹ ከአዲስ አበባ አልፎ በክልልም ተፈላጊነት እንዲጨምር አስችሏል ነው ያሉት።
በቀጣይም ተጨማሪ የማምረቻ ቦታና የጥሬ እቃ አቅርቦት ቢመቻች በማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪው ሰፊ ተሳትፎ በማድረግ የሚፈጠረውን የስራ ዕድል ቁጥር በእጥፍ ለማሳደግ ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።