በደቡብ ኦሞ ዞን በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት 582 የአረጋውያን ቤቶች ግንባታና እድሳት ይከናወናል -የዞኑ አስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኦሞ ዞን በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት 582 የአረጋውያን ቤቶች ግንባታና እድሳት ይከናወናል -የዞኑ አስተዳደር
ጂንካ ፤ ሐምሌ 14/2015(ኢዜአ)፡- በደቡብ ኦሞ ዞን በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ወጣቶችንና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ 582 የአረጋውያንና የአቅመ ደካሞችን ቤቶች ግንባታና እድሳት እንደሚከናወን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ አስታወቁ።
በዞኑ 10 ወረዳዎችና ሦስት ከተማ አስተዳደሮች በሚካሄደው በጎ አገልግሎት 145 ሺህ ወጣቶች የሚሳተፉ ሲሆን፣ ከ121 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ወጪ ለማዳንም እንደሚሰራ ተመላክቷል።
የዘንድሮው የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ ከዞኑ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ስመኝ ተስፋዬና ሌሎች አመራሮች ጋር በመሆን በደቡብ አሪ ወረዳ ጋዘር ከተማ የአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤትን በማደስ አስጀምረዋል።
አቶ ንጋቱ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማህበራዊ አንድነትን ከማጠናከር አኳያ የጎላ ሚና አለው።
በዞኑ በተያዘው የክረምት ወራት በሚካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶችን ግንባታና እድሳት ሥራ ይከናወናል ብለዋል።
በበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ 291 ቤቶች በአዲስ የሚገነቡ ሲሆኑ፣ ሌሎች 291 ቤቶች ደግሞ የእድሳት ሥራ እንደሚከናወንላቸው ገልጸዋል።
ዋና አስተዳዳሪው እንዳሉት የቤቶቹ ግንባታና እድሳት ሥራ እስከ ነሐሴ ወር መጨረሻ ድረስ ተጠናቆ ርክክብ ይደረጋል።
የደቡብ ኦሞ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ወሊ ሃይሌ በበኩላቸው በዘንድሮው የክረምት ወራት 145 ሺህ ወጣቶችን በተለያዩ የሥራ መስኮች ለማሳተፍ መታቀዱን ገልጸዋል።
ወጣቶቹ ከሚሳተፉባቸው የሥራ መስኮች በዋናነት የአረጋውያንና የአቅመ ደካማ ሰዎች ቤት እድሳትና ግንባታ፣ የችግኝ ተከላ፣ የከተማ ፅዳትና ውበት፣ የደም ልገሳና የትራፊክ ደህንነት ይገኙበታል።
በዞኑ 10 ወረዳዎች እና ሦስት የከተማ አስተዳደሮች በሚካሄደው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በተጨማሪ የመንግሥት ሠራተኞችና ከዞን እስከ ወረዳ ያሉ አመራሮች እንደሚሳተፉ አመልክተዋል።
የደቡብ አሪ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ግዳልቅ አልቂሚ በወረዳው 66 ቤቶችን በማደስ እስከ ነሐሴ ወር መጨረሻ ድረስ ለነዋሪዎቹ ለማስረከብ መታቀዱን ገልጸዋል።
ዛሬ ቤታቸው መታደስ የጀመረላቸው የጋዘር ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ዙፋን አድማሱ፤ ባለቤታቸውን በሞት ካጡበት ጊዜ ጀምሮ አራት ልጆቻቸውን ብቻቸውን እያሳደጉ መሆኑን ገልጸዋል።
ቋሚ የገቢ ምንጭ የሌላቸው በመሆኑ ልጆቻቸውን ለማኖርም ሆነ ቤታቸውን ለማደስ መቸገራቸውን ተናግረዋል።
"ችግሬን በማየት የዞኑ አመራሮችና ወጣቶች ቤቴን ለማደስ በመምጣታቸው ተደስቻለሁ'' ያሉት ወይዘሮ ዙፋን፣ ለተደረገላቸው ድጋፍም አመስግነዋል።