የኢትዮጵያንና የኮሪያ ሪፐብሊክን የጋራ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትንና አጋርነትን ለማሳደግ በቅርበት እየተሰራ ነው--አምባሳደር ደሴ ዳልኬ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያንና የኮሪያ ሪፐብሊክን የጋራ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትንና አጋርነትን ለማሳደግ በቅርበት እየተሰራ ነው--አምባሳደር ደሴ ዳልኬ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2015(ኢዜአ):- የኢትዮጵያንና የኮሪያ ሪፐብሊክን በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ አጋርነትን ለማሳደግ ከኮሪያ ሪፐብሊክ የገንዘብ ሚኒስቴርና የኮሪያ ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ገለጹ።
በኮሪያ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር ደሴ ዳልኬ በኮሪያ ሪፐብሊክ በተዘጋጀው የአፍሪካ እና ኮሪያ የኢኮኖሚ ልማት ትብብር ፈንድ ጉባኤ ላይ ተሳትፈዋል።
ጉባኤው በአፍሪካ እና በኮሪያ ሪፐብሊክ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትብብር ለማጠናከር ያለመ መሆኑም ተገልጿል።
በመድረኩም በአፍሪካ ለሚከናወኑ ፕሮጀክቶች በብድር አቅርቦትና በድጋፍ ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት ይገባል ብለዋል።
በኮሪያ ሪፐብሊክ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የኢትዮጵያንና የኮሪያ ሪፐብሊክን የጋራ ተጠቃሚነት እና አጋርነት ለማሳደግ ከኮሪያ ሪፐብሊክ የገንዘብ ሚኒስቴርና የኮሪያ ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የአፍሪካ እና ኮሪያ ሪፐብሊክ የኢኮኖሚ ትብብር መድረክ በአፍሪካ እና በኮሪያ ሪፐብሊክ መካከል የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ትብብር ማጠናከርን ታሳቢ በማድረግ እ.አ.አ ከ2006 ጀምሮ በየሁለት ዓመቱ በሚኒስትሮች ደረጃ የሚካሄድ መድረክ ነው።
መድረኩ ኮሪያ ሪፐብሊክ በኢኮኖሚው ዘርፍ ያላትን የኢኮኖሚ ዕድገት፣ በካምፓኒዎች መካከል እና በኢኮኖሚ ትብብር ዘርፍ ያሉ የፖሊሲ አማራጮች ዙሪያ ተሞክሮ መለዋወጥ የሚያስችል መሆኑም ተገልጿል።
ከመድረኩ ጎን ለጎንም አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ከአፍሪካ ሀገራት አምባሳደሮች፣ ከኮሪያ ሪፐብሊክ የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እና ከኮሪያ ሪፐብሊክ ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ ተወካዮች ጋር በትብብር እና አጋርነት ሊፈጠርባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።