የኢትዮጵያ የወጪ እና ገቢ ንግድን የሚያስተናግደው የኢትዮ-ጅቡቲ የመንገድ የደረጃ ማሻሻያ ሊደረግለት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የወጪ እና ገቢ ንግድን የሚያስተናግደው የኢትዮ-ጅቡቲ የመንገድ የደረጃ ማሻሻያ ሊደረግለት ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2015(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ የወጪ እና ገቢ ንግድን የሚያስተናግደው የኢትዮ-ጅቡቲ የመንገድ መስመር የደረጃ ማሻሻያ ሊደረግለት ነው።
ቀጣናዊ ትስስርን እና የገቢና ወጪ ንግድ ሎጂስቲክስን እንደሚያሳድግ የተነገረለት ይህው የመንገድ ደረጃ ማሳደግ ግንባታ ከዓለም ባንክ ግሩፕ የዓለም አቀፍ የልማት ማህበር (IDA) በተገኘ 730 ሚሊዮን ዶላር እንደሚከናወን ተገልጿል።
መንገዱ ኢትዮጵያን ከጅቡቲ ወደብ ጋር የሚያገናኝና ለቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ትስስር ያለው ፋይዳም እንዲሁ ከፍተኛ መሆኑ ተጠቁሟል።
የዓለም ባንክ ግሩፕ ባወጣው መረጃ የዚህ መንገድ ደረጃ ማሳደግ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ የያዘችውን ሁሉን አቀፍ ዕድገት የማፋጠን እና ቀጣናዊ ትስስርን የመፍጠር ትልም የሚደግፍ መሆኑን የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ መግለጻቸውን አትቷል።
የኢትዮጵያ 95 በመቶ የሚሆነው የገቢ እና ወጪ ንግድ የሚሳለጠው በዚሁ የመንገድ ኮሪደር መሆኑን የገለጸው መረጃው ፕሮጀክቱ አሁን ላይ ለወጪ እና ገቢ ንግድ ምልልስ አስቸጋሪ የሆነውን ከድሬዳዋ መኢሶ ያለውን መስመር ደረጃ እንደሚያካትትም ተገልጿል።
የድሬዳዋ መኢሶ መንገድ መስመር በመበላሸቱ አሽከርካሪዎች በሌላ መስመር ለመጠቀም በሚያደርጉት ጥረት ለተጨማሪ 146 ኪሎ ሜትር ጉዞ እንደሚገደዱም አስታውቋል።
ፕሮጀክቱ ይህንን ችግር ለመቅረፍም ከድሬዳዋ መኢሶ ያለውን መስመር ወደ ባለአራት መስመር ደረጃ ከፍ በማድረግ የትራንስፖርት ሰዓት መቀነስን፣ የመንገድ ደህንነት መጨመርን፣ የነዳጅ አጠቃቀምን፣ የጥገና ወጪን እና የከባቢ ብክለትን እንደሚቀንስ ተጠቁሟል።
በመሆኑም የመንገድ ማሻሻያ ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት እና ማህበራዊ ልማት የፋጥናል ተብሎ እንደሚታመንም ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ የወጪና ገቢ ንግድ ሎጀስቲክስ ቅልጥፍናን በማሳደግ የኢትዮጵያን የንግድ ተወዳዳሪነትን፣ በሎጀስቲክስ ዘርፉ መዋዕለ ነዋይ የማፍሰስ ፍላጎትን ማሳደግና የመንግስትን አቅም በማሳደግ መስመሩ ወደ ባቡር ግንባታ ደረጃ እንዲያድግ አስተዋጽኦ እንዳለው ተመላክቷል።
በተጨማሪም ፕሮጀክቱ የስራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች መስመሩን በመጠቀም ወደ ገቢ እና ወጪ ንግዱ እንዲቀላቀሉ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራልም ተብሏል።
ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያንና የቀንዱ አካባቢ ሀገራትን ትስስር ከማጠናከር ባለፈ የንግድ ልውውጡ መጠን እንዲያድግ፣ ለስራ ዕድል ፈጠራ እና የቁሳቁስ ብሎም የህዝብ እንቅስቃሴን እንደሚያሳድግ በዓለም ባንክ ግሩፕ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን ዳይሬክተር ኦስማኔ ዲዮን ገልጸዋል።
በዓለም ባንክ ግሩፕ የምስራቅ አፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ ቀጣናዊ ቅንጅት ዳይሬክተር ቡቴና ጉርማዚ በበኩላቸው ይህ ፕሮጀክት ባንኩ በአፍሪካ ቀንድ ከሚያደርጋቸው የልማት ፕሮጀክቶች መካከል ቀዳሚው መሆኑን ጠቁመዋል።