ቀጥታ፡

በዓለም የውሃ ስፖርቶች ሻምፒዮና የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ ወደ ጃፓን አመራ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2015(ኢዜአ):- በጃፓን እየተካሄደ በሚገኘው 20ኛው የዓለም የውሃ ስፖርቶች ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው ልዑክ ትናንት ወደ ስፍራው አቅንቷል።

ሻምፒዮናው ከሐምሌ 7/2015 ጀምሮ በፎኮካ እየተከናወነ ሲሆን ከ195 አገራት የተውጣጡ 2 ሺህ 392 ስፖርተኞች ተሳታፊ ናቸው።

ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው በአንድ ወንድ እና በአንድ ሴት ስፖርተኞች በውሃ ዋና ስፖርት ትወከላለች።

በውድድሩ ላይ የሚሳተፈው ልዑክ በትናንትናው ዕለት ሽኝት ተደርጎለታል።

በሽኝት ስነ ስርዓቱ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ ውሃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መሰረት ደምስ እና የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ተገኝተዋል።

ለዓለም የውሃ ስፖርት ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተወዳዳሪዎች የተመረጡት ከሁሉም ክልሎች ተወዳድረው የተሻለ ሰዓት ያስመዘገቡ መሆናቸው የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ገልጸዋል።

ስፖርተኞቹ ለውድድሩ ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውንም ጨምረው አመልክተዋል።


 

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት “ኢትዮጵያ አሸናፊ አገር ናት እናንተም ያላችሁን አቅም በመጠቀም የሞራል የበላይነት በመውሰድ አገራችሁን ከፍ አድርጋችሁ በድል እንድትመለሱ አደራ እላለሁ” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡


 

20ኛው የዓለም የውሃ ስፖርቶች ሻምፒዮና እስከ ሐምሌ 23/2015 ይቆያል።

በሻምፒዮናው ላይ የሚሳተፉት ስፖርተኞች የተሻለ ውጤት ካመጡ እ.አ.አ በ2024 በፈረንሳይ ፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የመሳተፍ እድል ያገኛሉ።

የዓለም የውሃ ስፖርቶች ሻምፒዮና በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ ውድድር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም