ምሩቃን ሥራ ፈጣሪ ለመሆን መትጋት ይጠበቅባችኋል- ፕሮፌሰር አሰፋ አስማረ - ኢዜአ አማርኛ
ምሩቃን ሥራ ፈጣሪ ለመሆን መትጋት ይጠበቅባችኋል- ፕሮፌሰር አሰፋ አስማረ
ጂንካ ሐምሌ 13 ቀን 2015 (ኢዜአ) ምሩቃን አቅማቸውን በመጠቀም ስራ ፈጣሪ ለመሆን መትጋት እንደሚጠበቅባቸው የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ፕሮፌሰር አሰፋ አስማረ አሳሳቡ።
ዩኒቨርሲቲው በቅድመ ምረቃ መርሀ ግብር በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 501 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።
የኢትዮጵያ ፕሮፌሰሮች ካውንስል አባልና የዩኒቨርስቲው የሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ፕሮፌሰር አሰፋ አስማረ በምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዳሉት ተመራቂዎች የመንግስት ስራ ብቻ ጠባቂዎች ከመሆን ይልቅ አቅማቸውን ተጠቅመው ስራ ፈጣሪ ለመሆን መትጋት ይኖርባቸዋል።
"ለዚህ ደግሞ የይቻላል ስሜትን ከተስፋ ጋር መሰነቅ ይገባል" ያሉት ፕሮፌሰር አሰፋ በዚህም ከራሳቸው አልፎ ሌሎችንም የሚጠቅሙ እንዲሆኑ አሳስበዋል ።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የታደሙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ወይዘሮ አብዮት ደለለኝ በበኩላቸው "ዩኒቨርሲቲው በአርብቶ አደር አካባቢዎች የትምህርት ተደራሽነትን በማስፋት የትምህርት ተሳትፎውን ለማሳደግ የጀመረው ስራ የሚያበረታታ ነው" ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከመደበኛ መርሃ ግብሩ በተጨማሪ በርቀትና በተከታታይ በዞኑ አርሶና አርብቶ አደር አካባቢዎች የትምህርት ተደራሽነቱን በማስፋት የትምህርት ዕድል ያላገኘውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል ።
"ዩኒቨርሲቲው ይህንን ውጤታማ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል" ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው በሚያካሂዳቸው የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎቶች በተለይም በትምህርትና ግብርና ዘርፍ ያለውን አቅም ከማውጣት አንጻር የሚያከናውናቸው አበረታች ሥራዎች መኖራቸውን የጠቀሱት ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ወይዘሮ ጎይቲ ዋንጮ ናቸው።
በአካባቢው የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋትና በሚሰራቸው የጥናትና ምርምር ስራዎች ማህበረሰቡን በተጨባጭ ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ዩኒቨርሲቲው በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በማስወገድ የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ከማሳደግ ረገድ ያለውን ክፍተት ለመድፈን የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ኩሴ ጉድሼ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን የአካባቢው ዕምቅ ሀብትን ወደ ልማት በመቀየር ኢኮኖሚ ለማመንጨት የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን እያካሄደ መሆኑን ገልጸዋል ።
"ዩኒቨርሲቲው በተለይ በግብርና፣ ቱሪዝም፣ አገር-በቀል ዕውቀቶች እና በግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ላይ አተኩሮ እየሰራ ነው" ብለዋል ።
ዩኒቨርስቲው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የተጣለበትን የሰለጠነ የሰው ሀይል የማፍራት ተልእኮ በብቃት እየተወጣ እንደሚገኝ ገልፀው፣ በተለይም ያለበት የአርብቶ አደር አካባቢ የትምህርት ተሳትፎው እንዲያድግ ድርሻውን በመወጣት ላይ እንደሚገኝ ዶክተር ኩሴ አመልክተዋል።
በመደበኛነት ከሚያስተምራቸው ባሻገር በተከታታይ የትምህርትና ስልጠና መርሃ ግብር እንዲሁም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየደገፈ መሆኑን ተናግረዋል።
የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎችም በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው የቀሰሙትን በተሰማሩበት የስራ መስክ በተግባር በመለወጥ ማህበረሰባቸውን የሚጠቅም ስራ መስራት እንዳለባቸው ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል ።
ከተመራቂዎች መካከል በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ከአካውንቲንግ የትምህርት ክፍል 3 ነጥብ 92 በማምጣት በማዕረግ የተመረቀችው ተማሪ ማህደር በጋሻው "ጠንክሬ መስራቴ ስኬታማ አድርጎኛል" ብላለች። ባስመዘገበችው ውጤት ደስተኛ መሆኗን ገልፃ፣ ለስኬት ያበቋትን አመስግናለች።
በቀጣይ አዳዲስ ስራ በመፍጠር በዩኒቨርሲቲው ያገኘችውን እውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ማህበረሰቡን ለማገልገል መዘጋጀቷን ገልጻለች።