በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር በቆይታቸው የኢትዮጵያና ጃፓንን የቆየ መልካም ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር በቆይታቸው የኢትዮጵያና ጃፓንን የቆየ መልካም ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ ገለጹ
አዲስ አበባ ሐምሌ 13/2015(ኢዜአ):-አዲሱ በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ በጃፓን ቆይታቸው በኢትዮጵያና በጃፓን መካከል ያለውን የቆየ መልካም ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
አምባሳደሩ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለጃፓኑ ንጉስ ናሩሂቶ በንጉሠ ነገሥት ቤተ-መንግሥት በመገኘት አቅርበዋል።
በወቅቱም አምባሳደር ዳባ ደበሌ በቆይታቸው የኢትዮጵያና ጃፓንን የቆየ መልካም ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የጃፓኑ ንጉስ ናሩሂቶ በበኩላቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ የመልካም ምኞች መልዕክታቸውን አስተላልፈው አምባሳደሩ በጃፓን በሚኖራቸው ቆይታ የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ አረጋግጠዋል።
አምባሳደር ዳባ የሹመት ደብዳቤያቸውን ካቀረቡበት ሁነት ጎን ለጎን ከጃፓን የኢኮኖሚ፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ኒሺሙራ ያሱቶሺ ጋር ተወያይተዋል።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ መጎብኘታቸውንና ትልቅ የኢኮኖሚ አቅም ያላት ሀገር መሆኗን ገልፀው የኢትዮጵያ መንግስት የተፈጠሩ ግጭቶችን እልባት ለመስጠት የተከተለውን የሰላም አማራጭ አድንቀዋል።
ሚኒስትሩ በቀጣይም በኢኮኖሚ፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
አምባሳደር ዳባ ደበሌ በበኩላቸው በኢኮኖሚ፣ንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማሳደግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።