ቀጥታ፡

በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምን በማስፈን ልማት እንዲረጋገጥ የሚሰራ ኃይል እየተገነባ ነው - የተጠባባቂ ኃይል ጠቅላይ መምሪያ

አዲስ አበባ ሐምሌ 13/2015(ኢዜአ)፦ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምን በማስፈን ልማት እንዲረጋገጥ የሚሰራ ኃይል እየተገነባ መሆኑን የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ጠቅላይ መምሪያ አስታወቀ።

የምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ከአባል ሀገራቱና ከመምሪያው ለተውጣጡ 22 ሰልጣኞች በአዲስ አበባ ሲሰጥ የነበረው የተልዕኮ አፈፃፀም የተግባርና የንድፈ ሀሳብ ስልጠና ተጠናቋል፡፡

የመምሪያው የሎጂስቲክስ ኃላፊ ኮሎኔል አህመድ ኢሳ፤ መምሪያው ዓላማውን ለማሳካት በሎጂስቲክስ አቅርቦትና ግዳጅ አፈፃፀም ላይ ሲሰጠው የነበረው ስልጠና በስኬት ተጠናቋል ብለዋል፡፡

የተሰጠው ስልጠና የአባል ሀገራቱ ሃይል የመምሪያውን ተልዕኮ መፈጸምና ማስፈጸም የሚያስችላቸውን እውቀት፣ ክህሎትና ልምድ የሚያገኙበት መሆኑንም አብራርተዋል።

በመሆኑም በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምን በማስፈን ልማት እንዲረጋገጥ የሚሰራ ኃይል እየተገነባ መሆኑን ኮሎኔል አህመድ ተናግረዋል።

የሥልጠናው አስተባባሪ ኮሎኔል ሳሙኤል ምዳላ፤ ከመምሪያውና አባል ሀገራት የተውጣጡ ሰልጣኞች በተሰማሩበት ቦታ ሁሉ ውጤታማ ስራ ማከናወን የሚችሉበትን ልምድና ክህሎት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም በተግባርና በንድፈ ሀሳብ የተሰጣቸውን ስልጠና በብቃት በመወጣት ለቀጣይ ተልዕኮ ዝግጁ ናቸው ብለዋል።

በመከላከያ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍና ጎረቤት ሀገራት ጉዳዮች ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀነራል ሰብስቤ ዱባ፤ ኢትዮጵያ ከምሥራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል ጠቅላይ መምሪያ እና ጎረቤት ሀገራት ጋር በቅርበት መስራቷን ትቀጥላለች ብለዋል፡፡

በተለይም በቀጣናው ሽብርተኝነትን ለመከላከል፤ የህዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ጉዳዮችን ለመመከት በትብብርና በቁርጠኝነት እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም