በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ተሰብስቧል- የፕሮጀክቱ ጽህፈት ቤት - ኢዜአ አማርኛ
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ተሰብስቧል- የፕሮጀክቱ ጽህፈት ቤት
አዲስ አበባ ሀምሌ 13/2015(ኢዜአ)፡- በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
ለግድቡ ግንባታ የሕዝቡን ተሳትፎና ከገቢ አሰባሰብ አንፃር በበጀት ዓመቱ የነበረውን አጠቃላይ ክንውን በማስመልከት ኢዜአ የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍቅርተ ታምር ጋር ቆይታ አድርጓል።
እርሳቸው እንዳሉትም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለግድቡ ግንባታ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ የላቀ እንደነበር ጠቅሰዋል።
በአገር ቤትም ይሁን በውጭ ያሉ ወገኖች በተለያዩ አማራጮች ለግድቡ ግንባታ የላቀ ድጋፍና ትብብር ነበራቸው ሲሉም አስታውሰዋል።
በቦንድ ግዥ፣ በ8100 አጭር የጽሑፍ መልዕክት ገቢ ማሰባሰቢያ፣ በዲጂታል ገቢ ማሰባሰቢያ፣ በአካልና በተለያዩ አማራጮች የተጠናከረ ልገሳ አድርገዋል ብለዋል።
በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለግድቡ ግንባታ ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ገልፀዋል።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ጀምሮ እስካሁን ከ18 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን አስታውሰው፤ የሕዝቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል።
በድጋፉ በአገር ቤትም ይሁን በውጭ የሚኖሩ ወገኖች ጠንካራ ተሳትፎ መኖሩን አንስተው፤ በቀጣይም የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በቀጣይም ጽህፈት ቤቱ የኅብረተሰቡን ተሳትፎና የድጋፍ ማሰባሰቢያ አማራጮች በመጠቀም ግድቡን ከፍፃሜ ለማድረስ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።