ቀጥታ፡

በምንሰማራበት የስራ መስክ በመትጋት ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የእድገት ጎዳና ለማሻገር የድርሻችንን እንወጣለን-ተመራቂ ተማሪዎች

 

መቱ ሐምሌ 13/2015(ኢዜአ)፦ በትምህርታችን ውጤታማ ለመሆን እንደተጋነው ሁሉ በምንሰማራበት የስራ መስክ በመትጋት ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የእድገት ጎዳና ለማሻገር የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ የመቱ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች ገለጹ።

መቱ ዩኒቨርሲቲ በቅድመና ድህረ ምረቃ መርሀ ግብር 644 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።

የዛሬ ምርቃታቸው የብርቱ ጥረትና ትጋት ውጤት መሆኑን የተናገሩት ተመራቂ ተማሪዎቹ በስራ ዓለምም ውጤታማ ለመሆን እንደሚሰሩ ለኢዜአ ተናግረዋል።

“ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠውን የመውጫ ፈተና ለማለፍ ሌላ ድርብ ጥረት ይጠበቅብን ነበር” ያለችው ተመራቂ ደራርቱ ተስፋዬ “ዓላማችንን ለማሳካት በትጋትና በጽናት መስራት ነበረብን“ ብላለች።

ጥረቷና ትጋቷ የመውጫ ፈተናውን በከፍተኛ ውጤት ማጠናቀቅ እንዳስቻላት ገልጻ በስራ ዓለም የሚገጥሟትን ፈተናዎች በመቋቋምና በትጋት በመስራት ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሻገር ሀላፊነቷን እንደምትወጣ አመላክታለች።

በትምህርት ቆይታው ኮቪድ 19 ጨምሮ የተለያዩ ተግዳሮቶችን በመቋቋም በመውጫ ፈተናው ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ለምረቃ መብቃቱን የገለጸው ደግሞ ተመራቂ አንዋር መሀመድ ነው።

በፈተናው ጥሩ ውጤት ለማምጣት ጊዜውን በአግባቡ ከመጠቀም ጨምሮ ብርቱ ጥረት ማድረጉን ጠቁሞ ያለፈበትን ልምድ በመጠቀም ወደ ፊት በሚሰማራበት መስክ ውጤታማ በመሆን ለሀገር እድገት የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

የዋንጫ ተሸላሚ የሚላታ አበራ በበኩሉ በተመረቀበት የትምህርት መስክ ባገኘዉ ዕውቀትና ክህሎት በትጋትና በፅኑ ታታሪነት ስሜት በመስራት ሕዝቡንና ሀገሩን በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

የመቱ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር እንደገና አበበ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት ተመራማሪዎች በውስጣቸው ያለውን የመለወጥ ኃይል በጥናትና ምርምር፣ በፈጠራ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ማኅበራዊ ተሳትፎን በማጎልበት የሕዝባቸውን ኑሮና ሀገራቸውን ለመለወጥ እንዲያውሉ አስገንዝበዋል።


 

የዕለቱ የክብር እንግዳ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና የመቱ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ አባል ዶክተር ዲማ ኖጎ ተመራቂዎች ሀገሪቱን የምትረከቡት ትልቅ ኃላፊነት የሚጠብቃችሁ ትውልዶች እንደመሆናችሁ ይህንን ኃላፊነትም በትልቅ ታማኝነትና የሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ መቀበል ይጠበቅባችኋል” ብለዋል።


 

“ትጋትና ፅናትን ደግሞ ይህንን የምትወጡበት መሳሪያ አድርጋችሁ መያዝ ይኖርባችኋል” ሲሉ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም