23ኛው ሶፊ ማልት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ምዝገባ በነገው እለት ይጀመራል

አዲስ አበባ ሀምሌ 13/2015(ኢዜአ) 23ኛው ሶፊ ማልት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ምዝገባ በነገው እለት ይጀመራል።

በ23ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 45 ሺህ ሰው እንደሚሳተፉ ተገልጿል።

23ኛውን ሶፊ ማልት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ምዝገባና ሌሎች ዝግጅቶች በተመለከተ መግለጫ ተሰጥቷል።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መሥራች  አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በዚሁ ጊዜ፤ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሩጫም በላይ ነው ብሏል።

ታላቁ ሩጫ ኢትዮጵያዊያንን እያሰባሰበ ልዩ ድምቀት የሚታይበት መሆኑንም እንዲሁ።  

ታላቁ ሩጫ የተሳካ ሩጫ በማዘጋጀት አርአያ መሆን የቻለ ስፖርታዊ ክንውን መሆኑንም ተናግሯል።   

ይህንንም ተከትሎ 23ኛው ሶፊ ማልት ታላቁ ሩጫ በቀጣይ ዓመት ህዳር ወር ላይ እንደሚካሄድ ገልጿል። 

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ኦፕሬሽን ዳይሬክተር ዳግም ተሾመ በበኩላቸው በ2016 ዓ.ም በሚካሄደው ሩጫ 45 ሺህ ሰው እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

በሩጫው ለመሳተፍ ከነገ ሐምሌ 14 ቀን 2015  ዓ.ም ጀምሮ ምዝገባ እንደሚጀመር ተናግረዋል።

ምዝገባውን በቴሌብር አልያም በአካል ለሚመዘገቡ ተሳታፊዎች ደግሞ በተመረጡ የዳሽን ባንክ ቅርንጫፎች በኩል ማካሄድ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም