ቀጥታ፡

ምሩቃን ራሳቸውን ከሙስናና ብልሹ አሰራር በመጠበቅ አገርና ህዝብን በታማኝነት ሊያገለግሉ ይገባል--ዶከተር ንጉስ ታደሰ

ደብረብርሀን  ሐምሌ 13/2015(ኢዜአ) ምሩቃን በቀጣይ ወደ ስራ ሲሰማሩ ራሳቸውን ከሙስናና ብልሹ አሰራር በመጠበቅ አገርና ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል እንዳለባቸው የደብረብርሀን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶከተር ንጉስ ታደሰ አስገነዘቡ።

ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ድግሪ ያሰለጠናቸውን 2ሺህ 143 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ንጉስ ታደሰ እንደገለጹት ምሩቃን ካለው ውስን ሀብት በማካፈል ያስተማራቸውን አገርና ህዝብ መካስ አለባቸው።

በእዚህም በቀጣይ ወደ ሥራ ሲገቡ ከሙስናና ከብልሹ አሰራር በፀዳ፣ በቅንነትና በታማኝነት አገርና ህዝብን ሊያገለግሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ በ2022 ዓ.ም በተግባር ተኮር ትምህርትና ምርምር ግንባር ቀደም ዩኒቨርሲቲ ለመሆን ራዕይ አንግቦ እየሰራ መሆኑንም ዶክተር ንጉስ ገልጸዋል።

በዚህም ለኢንጂነሪግ እና ቴክኖሎጂ፣ ለህክምናና ጤና ሳይንስ እንዲሁም ለግብርናና ኢኮኖሚክስ የትምህርት መስኮች ይበልጥ ትኩረት በመስጠት የሽግግር ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የተዘጋጀውን አገር አቀፍ የመውጫ ፈተና ከወሰዱ 2ሺህ 798 የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መካከል 1ሺህ 800 የሚሆኑት የማለፊያ ውጤት ማግኘታቸውን ዶክተር ንጉስ ተናግረዋል።

የእለቱ የክብር እንግዳ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ይፍሩ ታፈሰ በበኩላቸው፣ እውቀትና ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ሀይል ለሀገር እድገት ወሳኝ ነው ብለዋል።


 

ትምህርት ለአንድ ሀገር እድገት ወሳኝ በመሆኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የለውጥ ሀሳቦችን ከማፍለቅ በተጨማሪ መልካም አርአያ የሚሆኑ ብቁ ዜጎችን ማፍራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች የዴሞክራሲ አስተሳሰቦችና የቴክኖሎጂ መፍለቂያ እንዲሁም የባህላዊ እሴቶች መጎልበቻ መሆን እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

ምሩቃን ተማሪዎች የህዝቦች የመተሳሰብ፣ የመቻቻልና የአብሮነት ባህል እንዲጎለብት የድርሻቸውን እንዲወጡም ዶክተር ይፍሩ አሳስበዋል።

በዩኒቨርሲቲው በፋርማሲ ትምህርት 3 ነጥብ 99 በማምጣት የተመረቀችው አሚና ሀሰን በበኩሏ፣  "ችግሮችን ተጋፍጦ ለውጤት የመብቃትን ያህል የሚያስደስት ነገር የለም" ብላለች።


 

ለዛሬው ውጤት ለመብቃት የተለያዩ ውጣውረዶችን ማሳለፏን ገልጻ፣ ጠንክራ በመማሯ ለውጤት መብቃቷንና በቀጣይም አገርና ህዝብን በቅንነት ለማገልገል መዘጋጀቷን ተናግራለች።  

በማቲማቲካል ሞዴሊይንግ በ3ኛ ድግሪ የተመረቁት ዶክተር እንግዳ እንድሪያስ በበኩላቸው በሀገሪቱ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና ብቁ ተማሪዎችን ለማሳለፍ እንደ ሀገር የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግሯል። 


 

በተለይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋም ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ሀይል ለማፍራት የሚከናወኑ ስራዎች በቀጣይ ሀገርና ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን ለማከናወን ያስችላሉ ብለዋል።

 እንደ አገር የሚከናወኑ የልማት፣ የሰላምና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን ለማሳለጥ ብቃቱ የተረጋጋጠ የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለእዚህ ደግሞ የተጀመረው የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት ጠቃሚ መሆኑን የገለጸው ደግሞ በሕግ ትምህርት ክፍል በመጀመሪያ ድግሪ የተመረቀው ሳሙኤል እንድርያስ ነው።

ደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 686ቱ ሴቶች መሆናቸው ታውቋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም