ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለአንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ እና ለሰው ልጆች ደኅንነት የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከተው ቢኒያም በለጠ የክብር ዶክትሬት ሰጠ  

አዲስ አበባ ሀምሌ 13/2015(ኢዜአ)፡- የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለአንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ እና ለሰው ልጆች ደኅንነት የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከተው ቢኒያም በለጠ የክብር ዶክትሬት ሰጠ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዓይነት ያሰለጠናቸውን ከ8 ሺህ በላይ ተማሪዎች በዛሬው እለት አስመርቋል።

በዚሁ መርሃ-ግብር ላይ በኪነ-ጥበብ ዘርፍ የላቀ አስተዋጽዖ ላበረከተው አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ እና በማኅበራዊ አገልግሎትና ለሰው ልጆች ደኅንነት የላቀ አስተዋጽዖ ላበረከተው ቢኒያም በለጠ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል።

በ1943 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተወልዶ ያደገው አርቲስት ደበበ እሸቱ ከ1948 እስከ 1957 ትምህርቱን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ጨርሶ በመቀጠል ከ1958 እስከ 1960 ዓ.ም በኢትዮጵያ አየር ኃይል አገልግሏል።

በመቀጠልም ከ1960 እስከ 1961 በደብረ ብርሃን መምህራን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት በመግባት በመምህርነት ሙያ ሰልጥኗል። 

በ1953 ዓ.ም. በብርጋዴር ጄነራል መንግሥቱ ነዋይ እና ወንድማቸው ግርማሜ ነዋይ መሪነት በተካሄደው የመንግሥት ግልበጣ ሽብር ወቅት ትምህርቱን አቋርጦ በኢሉባቦር ከአንድ ዓመት በላይ በእሥራት ቆይቷል።

መጀመሪያ በቴአትር ጥበብ መድረክ ላይ የወጣው በመንግስቱ ለማ በተጻፈው ያላቻ ጋብቻ ላይ ሲሆን፤ የጥበብ ሥራው አሻራውን ማኖሩን ከመቀጠሉ ባለፈ በጋዜጠኝነትም በሬድዮና በቴሌቪዥን በርካታ ሥራዎችን ሰርቷል።

አርቲስት ደበበ እሸቱ ከተወነባቸው ሥራዎቹ መካከል 'ያላቻ ጋብቻ'፣ 'ሮሚዮና ዡልየት'፣ 'ዳንዴው ጨቡዴ' እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ።

ከዚያ በኋላ በሀንጋሪ አገር ከወጋየሁ ንጋቱ ጋር ቴአትር በማጥናት ወደ አገሩ ተመልሶ ዘርፉን ከፍ ወዳለ ደረጃ አሸጋግሯል፡፡

በእንግሊዝኛ ከሰራቸው ፊልሞች መካከልም 'ዘ ሴይለር ፍሮም ጂብራልተር'፣ 'ጉማ'፣ 'ዘ አፍሪካን ስፓይ'፣ 'ዜልዳ'፣ 'ዘ ግሬቭ ዲገር' እና 'ዘ ግሬት ሪቤሊየን ' ይጠቀሳሉ።

ሆሊውድ በተሠራው 'ሻፍት ኢን አፍሪካ' በተሰኘው ፊልም ላይ በመሳተፍም ስሙን በደማቁ ጽፏል።

ከዚህ በላይ በሀገር ፍቅር ቴአትር እንደ ዋነኛ ዳይሬክተር፣ በመረጃ ሚኒስቴር እንደ ጋዜጠኛ፣ እና ከስብሐት ገብረእግዚአብሔር ጋር በቁም ነገር መጽሔት በባለቤትነትና አዘጋጅነት አገልግሏል።

ለአፍሪካ ቴአትር ስላደረገው አስተዋጽዖም በ1991 ዓ.ም. ከቦስተን ከተማ እና በ1994 ከአትላንታ ከተማ በአሜሪካ ሽልማት ተቀብሏል።

ከዚህ በላይ በ1994 ዓ.ም. የጣይቱ ሽልማት የተበረከተለት ሲሆን፤ ደበበ እሸቱ በሀገር ፍቅርና በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ (የአሁኑ ብሔራዊ ቴአትር) መድረክ ላይ ለረዥም ዓመታት በተዋናይነትና በአዘጋጅነት ነግሷል። 

በመሆኑም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኪነ-ጥበብ ዘርፍ የላቀ አስተዋጽዖ ላበረከተው አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል።

“ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው” በሚለው ንግግሩ የሚታወቀውና በማኅበራዊ አገልግሎትና ለሰው ልጆች ደኅንነት የላቀ አስተዋጽዖ ላበረከተው የመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ቢኒያም በለጠም ዩኒቨርሲቲው የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል።

በትምህርቱ ጎበዝና ምስጉን የነበረው ወጣት ለቤተሰቦቹ ከአሥር ልጆች መካከል ስድስተኛ ሲሆን፤ ከቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ሲመረቅ ውጤቱ 4.00 ነበር። 

በዚህ የላቀ ውጤቱም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት የሕግ ትምህርት በማጥናት በሕግ ባለሙያነት በአገር ውስጥ አገልግሎ ወደ አገረ አሜሪካ ተጓዘ፡፡ 

በአሜሪካን ቆይታው  የተለያዩ ሥራዎችን ሲሰራ ቆይቶ ሁለተኛ ዲግሪውን በNon-profit management and development አገኘ፡፡

በ1970 ዓ.ም ከእናቱ ጽጌ በቀለ እና ከአባቱ በለጠ አዲስ በአዲስ አበባ የተወለደው እና “ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው”  በሚለው ድንቅ አባባሉ ይታወቃል።  

በአገረ አሜሪካ የተማረውን እውቀት እና ያጠራቀመውን ገንዘብ ይዞ አስታዋሽ ላጡ ሊደርስ የቅንጦት እና የምቾት ሕይወቱን በመተው ወደ አገር ቤት ተመለሰ፡፡

እናም በ1992/93 ዓ.ም መቄዶንያ የተሰኘ የአረጋውያን መርጃ ማዕከል በመክፈት 40 ደጋፊ ያጡ ሰዎችን በወላጆቹ ቤት ማኖር ጀመረ፡፡ 

መቄዶንያም አሁን ላይ በመላ ሀገሪቱ 25 ቅርንጫፎቹን በመክፈት ከ7 ሺህ 500 በላይ አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማንን በመቀበል እየተንከባከበ ይገኛል፡፡

በመሆኑም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማኅበራዊ አገልግሎትና ለሰው ልጆች ደኅንነት ላደረገው የላቀ አስተዋጽዖ የክብር ዶክትሬት ሰጥቶታል።

በተመሳሳይ እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ  ለድምጻዊት እጅጋየሁ ሽባባው(ጂጂ) የክብር ዶክትሬት አበርክቶላታል።

ዩኒቨርሲቲው ለጂጂ የክብር ዶክትሬቱን የሰጠው የኢትዮጵያን ባህልና ሙዚቃ ለዓለም በማስተዋወቅ እንዲሁም በኪነ ጥበብ የአዊን ሕዝብ ቋንቋ እና ባህል በማሳደግ ላበረከተችው አስተዋፅኦ መሆኑን ገልጿል።

የክብር ዶክትሬቱን የእጅጋየሁ ሽባባው ቤተሰቦች ተቀብለዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም