የኩላሊት ሕመምተኞችንና አንጋፋ አትሌቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የሕክምና እና የገበያ ማዕከል ግንባታ ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኩላሊት ሕመምተኞችንና አንጋፋ አትሌቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የሕክምና እና የገበያ ማዕከል ግንባታ ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ ሐምሌ 13/2015(ኢዜአ):- የኩላሊት ሕመምተኞችንና አንጋፋ አትሌቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የሕክምና እና የገበያ ማዕከል ግንባታ ፕሮጀክት ዛሬ ይፋ ተደርጓል።
ፕሮጀክቱን ይፋ ያደረጉት የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት እና የኢትዮጵያ አረንጓዴ ጎርፍ አትሌቲክስ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ሲሆኑ በጋራ ሕንጻ ገንብተው መጠቀም የሚያስችላቸው መሆኑ ተመልክቷል።
የኩላሊት ህመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ የፕሮጀክቱ አላማ በኩላሊት ሕክምና እጦት ለሚሰቃዩ ዜጎች እፎይታ መስጠት መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ በአዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቡልጋሪያ ኤምባሲ አካባቢ የሚገነባ ሕንጻን ያካተተ መሆኑንና የኩላሊት ሕክምና የሚሰጥበትና በችግር ላይ ለሚገኙ አንጋፋ አትሌቶች ገቢ ማስገኛነት የሚውል ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አረንጓዴ ጎርፍ አትሌቲክስ የበጎ አድራጎት ድርጅት ስራ አስኪያጅ አትሌት መልካሙ ተገኝ ፕሮጀክቱ ለአገር ውለታ የዋሉ አንጋፋ አትሌቶችን ከመደገፍ ባለፈ በኩላሊት ሕመም የሚሰቃዩ ዜጎችን የሚታደግ እንደሆነም ተናግረዋል።
ለማዕከሉ እውን መሆንና ለአገር ውለታ የዋሉ አትሌቶችን በሕይወት እያሉ ለማገዝ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ተወካይ አቶ ታሪኩ እሸቱ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ለበጎ አላማ በአንድነት መቆምን የሚያሳይ መሆኑንና ቢሮው ለፕሮጀክቱ እውን መሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።