ቀጥታ፡

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በአገራዊና ዜጎች ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ

አዲስ አበባ ሐምሌ 13/2015 (ኢዜአ):-በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በአገራዊና ዜጎች ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ በተጠናከረ መልኩ እንዲያስቀጥሉ ጥሪ ቀረበ።

ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የተወጣጣ ልዑክ በደቡብ አፍሪካና ሌሎች ደቡባዊ አፍሪካ አገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት አጠቃላይ ሁኔታ እና አገራዊ ተሳትፏቸውን የተመለከተ ቅኝት በማድረግ ላይ ነው።

ልዑኩ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መሪዎች ጋር በአገራዊ እና በዜጎች ጉዳዮች ላይም ምክክር አካሄዷል።

በውይይቱ ላይ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ከድር(ዶ/ር) ተሳትፈዋል።

በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች እና አካታች ሀገራዊ የምክክር መድረኮችን በማካሄድ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ጥረት አስመልክቶ በልዑኩ አባላት ገለጻ ተደርጓል።

የልዑኩ መሪ አቶ ወንድሙ ገዛኸኝ የሃይማኖት ተቋማት በአገር ሰላም ግንባታና ትውልድን በመልካም ስነምግባርና እሴቶች በማነጽ እንዲሁም የዜጎችን መስተጋብር በማጎልበት የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ በገጠማት ወቅት የሃይማኖት አባቶች ተከታዮቻቸውን በማስተባባር ላከናወኑት ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበው ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በምክክሩ የተሳተፉ የሃይማኖት አባቶች በበኩላቸው በአገራዊ እና ዜጎች ጉዳዮች ላይ እያበረከቱ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ ገልጸዋል።

የሃይማኖት አባቶቹ ከአገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እያጋጠማቸው ስላሉ ተግዳሮቶች አንስተዋል።

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ከድር(ዶ/ር) በልዑኩ አባላት እና ሃይማኖት አባቶች የተነሱት ሃሳቦች ላይ በሰጡት አስተያየት ለቀጣይ የተጠናከረ የቅንጅት እንቅስቃሴ በግብአትነት የሚገልግሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በውይይቱ ለተነሱ ዋና ዋና ጉዳዮች መፍትሔ ለማበጀት መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።

በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በአገራዊና ዜጎች ጉዳዮች ላይ ከሚሲዮኑ ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም