ቀጥታ፡

በትግራይ ክልል ወርቅን ጨምሮ በማዕድን ፍለጋና ማምረት ላይ የነበሩ ኩባንያዎች በቅርቡ ስራ ይጀምራሉ-ማዕድን ሚኒስቴር 

አዲስ አበባ ሀምሌ 13/2015(ኢዜአ)፡- በትግራይ ክልል ወርቅን ጨምሮ በማዕድን ፍለጋና ማምረት ላይ የነበሩ ኩባንያዎች በቅርቡ ስራቸውን መጀመር የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት የማእድን ዘርፉን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ስራዎች ከመስተጓጎላቸው ባለፈ ጉዳትም አስተናግደዋል።

ከሰላም ስምምነቱ  በኋላ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተከትሎ የልማት፣ የአገልግሎትና ሌሎችም መስኮች የስራ እንቅስቃሴ በጥሩ ሁኔታ ዳግም ተጀምሯል።

በትግራይ ክልል በተለይም በወርቅና ሌሎችም ማዕድናት ፍለጋና ምርት ላይ ያለውን እንቅስቃሴ በተመለከተ ኢዜአ ከማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ ሚሊዮን ማቴዎስ ጋር ቆይታ አድርጓል።

በክልሉ የተለያዩ በዘርፉ ልማትና የፍለጋ ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በጦርነቱ ሳቢያ ስራቸውን ማካሄድ ተቸግረው መቆየታቸውን አስታውሰው አሁን ላይ ለመጀመር የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

መንግስትና ህወሓት ጦርነቱን ለማቆምና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈራረሙት ስምምነት እንደ ሀገር በማዕድን ዘርፍ ለተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ትልቅ እፎይታን ያመጣ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

በመሆኑም በትግራይ ክልል ወርቅ፣ ሲሚንቶና ሌሎችም የማዕድን ማምረትና ፍለጋ ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ወደ ስራ እንዲመለሱ ምቹ ሁኔታዎች የተፈጠሩላቸው መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

በክልሉ የሚገኘው መሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ አስቀድሞ ስራ መጀመሩን አስታውሰው ለሌሎችም ስራ ለመጀመር የሚያስችላቸውን እንቅስቃሴ ጀምረዋል ነው ያሉት።

በክልሉ ቀደም ሲል አንዳንድ የወርቅ ፋብሪካዎች እስከ 900 ኪሎ ግራም ወርቅ በማምረት ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረባቸውን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የማምረት አቅምን መልሶ ለማምጣት ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

ለዚህም ሽሬ የሚገኘው የወርቅ ባንክ መልሶ እንዲከፈትና ባለሙያዎች እንዲመደቡ በማድረግ የወርቅ ግዥ ስርዓቱ እንዲጀመር ወደ ተግባር መገባቱን አንስተዋል።

ከዚህም ባለፈ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በህገወጥ መንገድ ገብተው እያመረቱ በነበሩ ህገወጦች ላይ ጥብቅ እርምጃ መውሰዱን ተናግረዋል።

ህግን የማስከበር እርምጃው ህጋዊ ፈቃድ ለተሰጣቸው የማዕድን አምራቾችና ፍለጋ ላይ የተሰማሩ አካላት በመተማመን ወደ ስራ እንዲገቡ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ በክልሉ በዓለም የወርቅ ማዕድን ዘርፍ ታዋቂ የሆነው ኒውሞንት ኩባንያን ጨምሮ ሌሎችም ዓለም አቀፍ የማዕድን ኩባንያዎች ስራቸውን መልሰው በቅርቡ እንደሚጀምሩ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

ይህም ለሀገር ገፅታና ለዘርፉ መነቃቃት ትልቅ ሚና ያለው በመሆኑ ሚኒስቴሩ ለኩባንያዎቹ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም