ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአቪዬሽን ደኅንነትን በማስጠበቅ ረገድ በአፍሪካ ተምሳሌት እንደምትሆን ተገለጸ

አዲስ አበባ ሐምሌ 12/2015(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ዘርፍ ደኅንነትን በማስጠበቅ ረገድ እያከናወነች ያለችው ሥራዎች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን የአሜሪካ ትራንስፖርት ደኅንነት መስሪያ ቤት (TSA) ባደረገው አጠቃላይ የበረራ ደኅንነት የኦዲት ሥራ ማረጋገጡን ገልጿል ።

በብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሥር የሚገኘው የሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ የቦሌ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ በሁሉም ዘርፎች ያከናወኗቸው የተለያዩ የሪፎርም ትግበራ ሥራዎች ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ደኅንነቱን በማስጠበቅ በኩል አስተዋጽኦ አበርክቷል።

የአሜሪካ ትራንስፖርት ደኅንነት መስሪያ ቤት (Transportation Security Administration ) ከሃምሌ 10 ጀምሮ እስከ ሃምሌ 12 /2015 ዓም ድረስ ለተከታታይ ሶስት ቀናት በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ባካሄደው የበረራ ደኅንነት ልዩ የኦዲትና የፍተሻ ሥራ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያው ምንም አይነት የሴኪዩሪቲ ክፍተት ችግር ግኝት ሳይኖር አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡ ተመልክቷል ።

የአሜሪካ ትራንስፖርት ደኅንነት መስሪያ ቤት ልዑካን ቡድን የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሥር ለሚገኘው የአቪዬሽን ደኅንነት ዘርፍ በሠጠው ልዩ ትኩረት የሪፎርም ትግበራ ሥራዎች፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘመናዊ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት፤ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበርና በመቀናጀት ያከናወናቸው የደኅንነት ቁጥጥርና የፍተሻ ሥራዎች ለስኬቱ መገኘት ትልቅ ድርሻ እንደነበራቸውም ተገልጿል።

የአቪዬሽን ደኅንነትስ ዘርፉ የተገኘው ውጤትም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተወዳዳሪነትና ተመራጭነት ከማሳደጉም በላይ በቀጣይም ይበልጥ ተነሳሽነትን የሚፈጥር በመሆኑ የጠቆሙት በብሔራዊ መረጃና ደንነት አገልግሎት የሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ ዳይሬክተር አቶ አስራት ቀጀላ ውጤቱ እንዲመጣ አስተዋጽኦ ላደረጉ የአገልግሎቱ ሠራተኞችና የባለድርሻ አካላት ታላቅ ምስጋና አቅርበዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም