ቀጥታ፡

አፍሪካ እና ሩሲያ በፖለቲካው ዘርፍ ያላቸው ጠንካራ ትብብር በኢኮኖሚው መስክ እያደገ መጥቷል - አምባሳደር ቻም ኡጋላ  ኡሪያት

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 12/2015(ኢዜአ)፦ አፍሪካ እና ሩሲያ በፖለቲካው ዘርፍ ያላቸው ጠንካራ ትብብር በኢኮኖሚው መስክ ጥሩ ሽግግር እያሳየ መምጣቱን በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ቻም ኡጋላ ኡሪያት ገለጹ። 

የሩሲያው የዜና አገልግሎት ስፑትኒክ ኢንተርናሽናል እህት ኩባንያ የሆነው የሚዲያ ተቋም ሮሲያ ሴጎድኒያ በተቋሙ ቅጥር ግቢ ውስጥ ያዘጋጀው የአፍሪካ ኤክስፖ ዛሬ ተጀምሯል። 

በኤክስፖው መክፈቻ ላይ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ባለስልጣናት እና ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል። 

በኤክስፖው ላይ የተገኙት በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ኡሪያት ቻም ኡጋላ ከስፑትኒክ አፍሪካ ጋር ቆይታ አድርገዋል። 

ሩሲያ ለረጅም ጊዜ የአፍሪካን አገራት በፖለቲካው መስክ ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷንና በቀጣዩ ሳምንት በሚካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ይህን ትብብር በኢኮኖሚው መስክ እንዲሸጋገር ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው አምባሳደር ኡሪያት ገልጸዋል። 

ሩሲያ ለረጅም ዘመናት ከአፍሪካ ጎን መቆሟን አውስተው ሶቪየት ሕብረት የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት ነጻ ለመውጣት ባደጉት ትግል ውስጥ ያደረገችውን ድጋፍ አንስተዋል።

ለአፍሪካ በዓለም አቀፍ መድረክ እያደረገች ያለው ድጋፍ መቀጠሉንና ጉባኤውም ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር በመከባበር ላይ የተመሰረተ ትብብር ለመፍጠር ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል። 

ጉባኤው አፍሪካ እና ሩሲያ በኢኮኖሚው ዘርፍ ያላቸውን ትብብር እንደሚያጠናክር እምነታቸውን መሆኑን ነው አምባሳደሩ የገለጹት። 

ጉባኤው ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ሁኔታ በፍጥነት እየተቀየረበት ያለበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንደሚካሄድ የገለጹት አምባሳደሩ የዓለም አገራት እጣ ፋንታ በራሳቸው እጅ ላይ ነው ብለዋል። 

ከዚህ አንጻር የአፍሪካ አገራት እና ሩሲያ በጋራ መስራት እንዳለባቸው ጠቅሰው ሁለቱን አካላት የሚያቀራርቡ ብዙ ሁኔታዎች እንዳሉና ትብብራቸውን ወደ ተሻለ ደረጃ መስራት እንደሚገባቸው አመልክተዋል። 

በሌላ በኩል ዛሬ በሩሲያ ሴጎድኒያ የተጀመረው የአፍሪካ ኤክስፖ በተመለከተ ኤክስፖውን ጨምሮ ሌሎች መርሐ-ግብሮች ኢትዮጵያ እና ሩሲያ ይበልጥ እርስ በእርሳቸው እንዲተዋወቁና ያላቸውን ራዕዮችና ሕልሞች አስመልክቶ ሀሳብ እንዲለዋወጡ እድል ከመፍጠር አኳያ በጣም ጠቃሚ መሆኑን ነው አምባሳደሩ ያብራሩት።

ሁለተኛው የአፍሪካ-ሩሲያ ጉባኤ ሐምሌ 20 እና 21/2015 በሩሲያ ቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ ይካሄዳል።

ጉባኤው በአፍሪካ አገራት እና ሩሲያ መካከል ያለውን ሁሉን አቀፍና ሚዛናዊ ትብብር ማጠናከር አላማ ያደረገ መሆኑን ስፑትኒክ በዘገባው አስፍሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም