ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል ላልተወሰነ ጊዜ የሚቆይ የሰዓት እላፊ ገደብ ተጣለ

አዲስ አበባ ሐምሌ 12/2015(ኢዜአ)፦በጋምቤላ ክልል ሁሉም አካባቢዎች ላልተወሰነ ጊዜ የሚተገበር የሰዓት እላፊ ገደብ ተጣለ።

ውሳኔው የተላለፈው የክልሉን ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ በማስመልከት ካቢኔው ዛሬ አመሻሹ ላይ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ነው።

በክልሉ ሰሞኑን በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከምሽቱ 1:00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ 12:00 ሰዓት ላልተወሰነ ጊዜ የሚተገበር የሰዓት እላፊ ገደብ መጣሉን አመልክቷል።

ከዛሬ ጀምሮ ከተመደቡ የጸጥታ ኃይል በስተቀር ከምሽቱ 1:00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ 12:00 ሰዓት ድረስ ማንኛውም ተሽከርካሪም ሆነ ሰው መንቀሳቀስ የተከለከለ መሆኑን የክልሉ መንግስት አስታውቋል።

ከተመደቡ የፀጥታ አካላት ውጪ የትኛውንም ጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማይቻልም ተወስኗል።

በሌላ በኩል ሁሉም የመንግስት ሰራተኛም ሆነ አገልግሎት ሰጪ የንግድ ተቋማት ከነገ ጀምሮ መደበኛ ስራቸውን እንዲያከናዉኑ ካቢኔው ውሳኔ አሳልፏል።

በክልሉ ለተፈጠረው የሰላም መደፍረስ እጁ ያለበት አመራርም ሆነ ሌላ አካል ተጣርቶ ተጠያቂ እንደሚደረግም ካቢኔው በውሳኔው አስታውቋል።

በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የተጣሉ ክልከላዎችን በማክበርና በማስከበር ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በሃላፊነት መንቀሳቀስ እንዳለበት ካቢኔው አሳስቧል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም