ቀጥታ፡

በህክምናው ዘርፍ  በሀገር ውስጥ አቅም የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል--ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ ሐምሌ 12/2015 (ኢዜአ):- በህክምናው ዘርፍ በሀገር ውስጥ አቅም መድሃኒቶችንና የህክምና መሳሪያዎችን ለማምረት የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሳይንስ ሙዚየም አገር አቀፍ የጤና አውደ ርዕይን ዛሬ ጎብኝተዋል።


 

በጤናው ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን አስመልክቶም በጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በጉብኝታቸው ህክምናን በጥራት ተደራሽ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን የሚደረገውን ጥረት ለመመልከት መቻላቸውን ገልጸዋል።

በሁሉም መስክ የተሻለች ሀገርን ለመገንባት ጤናማ ህብረተሰብ እጅግ አስፈላጊ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቷ፤ መንግስት በጤናው ዘርፍ እያካሄደ ያለው ስራ የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የጤና አጠባበቅ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ለማጠናከር፤ ከመንግስት ባሻገር የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ማደግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በአውደ ርዕዩ በአገር ውስጥ አቅም የህክምና መሳሪያዎችንና መድሃኒቶችን ለማምረት የሚደረገውን ጥረት ማየታቸውን በማንሳት፤ ይህም ለሀገር ተስፋ የሚሰጥ ነው ብለዋል።

በህክምናው ዘርፍ የተጀመሩ ተስፋ ሰጭ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አመላክተዋል።

የጤና አውደ ርዕይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰኔ 14 ቀን 2015 ዓ.ም በይፋ ለህዝብ ዕይታ ክፍት መደረጉ ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም