በጋምቤላ ክልል የልማት ቱሩፋትን ቀድሞ የሚያሳኩ መልካም ጅምሮች እንዳሉ መገንዘብ ችለናል -የፌዴራል ከፍተኛ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል የልማት ቱሩፋትን ቀድሞ የሚያሳኩ መልካም ጅምሮች እንዳሉ መገንዘብ ችለናል -የፌዴራል ከፍተኛ አመራሮች
ጋምቤላ ሐምሌ 12 / 2015(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የልማት ቱሩፋትን ቀድሞ ማሳካት የሚያስችሉ አቅምና መልካም የአፈፃፀም ጅምሮች እንዳሉ መገንዘብ መቻላቸውን የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች አስታወቁ።
በክልሉ ተሰማርተው ለአስር ቀናት የቆዩት የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች የድጋፍና ክትትል ስራዎችን አጠናቀው ተመልሰዋል።
ከአመራሮቹ መካከል የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካና የርዕዩተ ዓለም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዛዲግ አብርሃ እንደገለጹት፤ በጋምቤላ ክልል ያለው እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱን የማልማት አቅም ጭምር እንዳለው መረዳት ችለዋል።
የክልሉ አመራር ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ወደ ልማት ለመለወጥ ከሰራ ለአካባቢው ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያዊያን ሁሉ የሚተርፍ ሀብት ማፍራት ይቻላል ብለዋል።
በተለይም ኢትዮጵያውያን በገበታቸው የተመጣጠነ ምግብ የሚያገኙ ዜጎች የማድረግ ህልም ረዘም ያለ ጊዜ የፈጀና አሁንም ሰፊ ትግል የሚጠይቅ ቢሆንም ይህንን ለማሳካት ጥረቱ መቀጠሉን ተናግረዋል።
የጋምቤላ ክልል ካሉት የማር፣ የፍራፍሬ ፣የዓሳ፣ የእንስሳትና ሌሎች እምቅ አቅሞች አኳያ በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና የሌማት ቱሩፋቱን ቀድሞ የሚያሳኩ መልካም ጅምሮች እንዳሉ መገንዘባቸውን ገልጸዋል።
በጋምቤላ ክልል የሌማት ቱሩፋት መርሃ ግብርን ከማሳካት አኳያ ከሁሉም ክልሎች መቅደም የሚስችሉት አቅሞች ያሉትና በጥሩ ሂደት ላይ እንደሚያገኝ የገለጹት ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ዳባ ናቸው።
በተለይም በዶሮ፣ በወተት፣ በዓሳ፣ በፍራፍሬና በሌሎች ዘርፎች ግቡን ለማሳካት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዓለሙ አኖ በበኩላቸው፤ ጋምቤላ ክልል በሁሉም የተፈጥሮ ሀብቶች የታደለና ብዙ ሊሰራበት የሚገባ አካባቢ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም የሌማት ቱሩፋቱን እውን ለማድረግ ያለውን የዓሳና ሌላውንም የእንስሳት ሀብት የማዘመን ስራዎች ከተከናወኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግቡን እንደሚያሳካ እምነቴ ነው ብለዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ፤ በዘንድሮ ክረምት በተለይም እንደ ሀገር በታለሙት የልማት መስኮች ላይ የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ ትኩረት ተሰጥቶ ከሚሰራባቸው የልማት ዘርፎች መካከል የሌማት ቱሩፋት መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም በጓሮ አትክልት፣ በዓሳ፣ በማርና ሌሎችም ዘርፎች ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ከሐምሌ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ሲያካሂዱ የቆዩትን የድጋፍና ክትትል ስራዎች አጠናቀው ተመልሰዋል።