በአማራ ክልል ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን በመቆጣጠር ምርትን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማድረስና ገበያውን ለማረጋጋት ይሰራል--ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን በመቆጣጠር ምርትን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማድረስና ገበያውን ለማረጋጋት ይሰራል--ቢሮው
ደሴ ሐምሌ 12/2015(ኢዜአ) በአማራ ክልል ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን በመቆጣጠር ምርትን ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማድረስና ገበያውን ለማረጋጋት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የደቡብ ወሎ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ "ሰላማዊና ዘመናዊ ንግድ ለክልላችን ግንባታ" በሚል መሪ ሀሳብ የንግድ ቀንን በደሴ ከተማ በፓናል ውይይት አክብሯል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ፈንታው ፈጠነ እንደገለጹት፣ በክልሉ ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን በመቆጣጠር ምርትን ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማድረስና ገበያን ለማረጋጋት በቅንጅት እየተሰራ ነው።
ለዚህም በየደረጃው ጥምር ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፤ ህገ ወጥ ነጋዴዎች በህጋዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ከማድረግ ባለፈ አስተዳደራዊ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልፀዋል።
ከእዚህ በተጨማሪ ምርት በብዛት ካለበት አካባቢ የምርት እጥረት ወዳለበት በማድረስ ገበያውን የማረጋጋት ሥራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 479 ሚሊዮን ብር ተመድቦ ገበያ የማረጋጋት ሥራ ተሰርቷል።
በገበያ ማረጋጋት ሥራው የግብርና ምርት ብቻ ከ270 ሺህ ኩንታል በላይ ቀርቦ ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገዛ ተደርጓል።
"በተጨማሪም በ79 ከተሞች የቅዳሜና እሁድ ገበያን በማመቻቸት አምራቹና ሸማቹን በቀጥታ ማገናኘት በመቻሉ በደላሎች ይደርስ የነበረን ወከባን ማስቀረት ተችሏል፣ ቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።
በአዲሱ በጀት ዓመት ቅንጅታዊ ሥራውን በማጠናከር የኑሮ ውድነትን በተሻለ ለማርገብ ጥረቱ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ መንግስቴ በበኩላቸው በዞኑ ጤናማ የንግድ ስርዓት በመዘርጋት ህገ ወጥነትን ለመከላከልና ገበያውን ለማረጋጋት በቅንጅት እየተሰራ ነው።
የተቋቋመው ግብረ ኃይል ባደረገው ቁጥጥርና ክትትል በምርት ላይ ያለ አግባብ ዋጋ የጨመሩ፣ ምርት የደበቁ፣ ያለንግድ ፍቃድ ሲሰሩ የነበሩ፣ የምርት ጥራት ያጓደሉና በመሰል ህገ ወጥ ተግባራት የተሰማሩ መገኘታቸውን ገልጸዋል።
በእነዚህ ህገወጥ ተግባራት የተሳተፉ ከ14 ሺህ በላይ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱንም አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል።
በዚህም የንግድ ተቋማቸው የታሸገ፣ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸውና አስተዳደራዊ እርምጃ የተወሰደባቸው ከመኖራቸው ባለፈ ከባድ ህገ ወጥ ተግባር የፈጸሙ ከ50 በላይ ነጋዴዎች ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን አስረድተዋል።
በተጨማሪም ገበያውን ለማረጋጋት በተደረገ ጥረት 88 ሺህ ኩንታል የግብርናና 14 ሺህ ኩንታል የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ለማድረስ መቻሉን አቶ ተስፋዬ አመልክተዋል።
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ዘላለም ገበየሁ በበኩላቸው እንዳሉት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት አቅርቦትና ፍላጎትን ከማመጣጠን ባለፈ ህገ ወጥ ተግባራትን ተከታትሎ ማስቆም ይገባል።
ያለ አግባብ ምርት የሚከዝኑ፣ የሚደብቁ፣ ዋጋ የሚጨምሩና የውሸት ፕሮፓጋንዳ የሚያናፍሱትን እየለዩ እርምት መውሰድና ቀጣይነት ያለው አቅርቦት እንዲኖር በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
አልፎ አልፎ በመንግስት በተመጣጣኝ ዋጋ በሚቀርብላቸው ምርት ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ደግሞ በሀርቡ ከተማ በምግብ ቤት ሥራ የተሰማሩት ወይዘሮ ሰላምባች ይገዙ ናቸው።
ጅምሩ መልካም ቢሆንም አሁንም ብዙ መስራት ይጠይቃል ያሉት ወይዘሮዋ፣ "ህገ ወጥነትን በመቆጣጠር ገበያውን ለማረጋጋት ከሁላችንም ብዙ ይጠበቃል" ብለዋል።
በፓናል ውይይቱ የክልል፣ የዞን እና የወረዳ አመራሮችን ጨምሮ የንግዱ ማህበረሰብና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ተሳትፈዋል።