የሕዳሴ ግድቡን የአገልግሎት ጊዜ ለማራዘም ችግኝ የመትከልና የመንከባከብ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የሕዳሴ ግድቡን የአገልግሎት ጊዜ ለማራዘም ችግኝ የመትከልና የመንከባከብ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ ሐምሌ 12/2015(ኢዜአ):- የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአገልግሎት ጊዜ ለማራዘም ችግኝ የመትከል፣ የመንከባከብ እና ሌሎች የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣንና ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመሆን በኦሮሚያ ክልል በጫንጮ ሱሉልታ ወረዳ ችግኝ ተክሏል።
በችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩ ላይ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ሠራተኞችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍቅርተ ታምር በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ወደ ዓባይ ግድብ በሚፈሱ ወንዞች አካባቢ ችግኝ መትከል እና እርከን መሥራት ግድቡ በደለል እንዳይሞላ የማድረግ አቅም አለው።
ችግኝ መትከልና የአካባቢ ጥበቃዎችን በስፋት ማካሄድ የግድቡን የአገልግሎት ጊዜ ለማራዘም ወሳኝ በመሆኑ የአረንጓዴ አሻራና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ገለፃ አረንጓዴ አሻራና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች የመሬትን ለምነት ከመጨመር ባሻገር ምንጮችን የማጎልበት፣ የደረቁ ወንዞች መልሶ እንዲያገግሙ ማድረግ ትልቅ ሚና ያላቸው በመሆኑ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተለይም በዓባይ ተፋሰስ ውስጥ ያሉ አርሶ አደሮችና ነዋሪዎች የአካባቢው ሥነ-ምህዳርን መጠበቅ ላይ የተጠናከረ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ነው ጥሪ ያቀረቡት።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው፤ ባለሥልጣኑ ከበርካታ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመሆን የሕዳሴ ግድቡ የደረሰበትን ደረጃ መጎብኘቱን ጠቅሰው፤ ግድቡ የደረሰበት ደረጃ አስደስቶናል ብለዋል።
በቀጣይም በተሻለ መልኩ ለግድቡ በኃብት፣ በዲፕሎማሲ በሌሎችም መስኮች ድጋፍ ማድረግ አለብን ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ለዚህም በቁርጠኝነት እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።
አቶ ፋሲካው እንደሚሉት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ለሥነ-ምህዳር መጠበቅ ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ በመሆኑ ባለሥልጣኑ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመሆን የበኩሉን ሚና እየተወጣ ነው።
ዛሬ በኦሮሚያ ክልል ጫንጮ ላይ የተከልነው ችግኝ ለዚህ ማሳያ ነው ሲሉ የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ችግኝ ተከላና የእንክብካቤ ሥራዎች ወደ ፊትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ ችግኞችን መትከል ብቻ ግብ አይደለም፤ ዘላቂነት ያለው እንክብካቤ ያስፈልጋል ብለዋል።
ተሳታፊዎቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ የነገዋን ኢትዮጵያ ተስፋ የሚያለመልም የተሻለ አገር የማድረግ አቅም ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ተሳታፊ በመሆናችን ደስታችን ወደር የለውም ነው ያሉት።