ቀጥታ፡

በመጀመሪያው ዙር 75 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል- የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን

አዲስ አበባ ሐምሌ 12/2015(ኢዜአ) በመጀመሪያው ዙር መርሃ ግብር 75 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉን የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ገለጸ፡፡

የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ በማስፈታት መልሶ ለማቋቋም በሚያደረገው ጥረት መገናኛ ብዙሃን ለሰላምና የሀገር ግንባታ እገዛ እንዲያደርጉም ተጠይቋል።

በዚህ ሂደት የመገናኛ ብዙሃን የሚኖራቸውን ሚና በተመለከተ ከዘርፉ ባለሙያዎችና የሥራ ኃላፊዎች ጋር በአዲስ አበባ ውይይት ተደርጓል፡፡


 

የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፤ ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በኋላ ከሁለት ዓመታት በላይ የዘለቀው ግጭት እልባት ማግኘቱን አስታውሰዋል።

ስምምነቱ ከያዛቸው ጭብጦች መካከል በውጊያና ተዋጊዎችን በመደገፍ ላይ ተሳትፎ የነበራቸውን ሁሉ ትጥቅ በማስፈታት ተኩስ እንዲቆም ማድረግና በዘላቂነት መልሶ ማቋቋም ቅድሚያ የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።

በመሆኑም የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 525/2015 ተቋቁሞ በይፋ ሥራ ከጀመረ በኋላ ትርጉም ያለው ሥራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በስምንት ክልሎች ካሉ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በተደረገ ማጣራት 371 ሺህ 971 የቀድሞ ተዋጊዎች መኖራቸውን አረጋግጠናል ነው ያሉት።

በመጀመሪያው ዙር እስከ ፈረንጆቹ 2023 መጨረሻ 75 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ ለማቋቋም አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

አሁን ላይ የቀድሞ ተዋጊዎቹ የሚቆዩበትን ካምፕ በማዘጋጀት፣ አስፈላጊውን ሃብት በማሰባሰብና የሥልጠና ቁሳቁሶችን በማሟላት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር ከ1990 ወዲህ በዓለም ላይ ከ60 ጊዜ በላይ ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም ስራ መከናወኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ከደርግ ውድቀት ማግስት በሺዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎችን መልሳ ማቋቋሟን ጠቅሰዋል።

የቀድሞ ተዋጊዎች በሰላም፣ ልማትና ሀገር ግንባታ ሂደት ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ መልሶ ማቋቋም ሥራ ይከናወናል ብለዋል፡፡

"በትግራይ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ እና ሌሎች ክልሎችም ያወያየናቸው የቀድሞ ተዋጊዎች በቶሎ ተቋቁመው ወደ መደበኛ ህይወታቸው የመመለስ ፍላጎት እንዳላቸው አረጋግጠውልናል"ብለዋል።

የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ መደበኛ ህይወታቸው መመለስ "ጦርነት በቃን ችግሮችን በሰላም መፍታት" የሚሉ ኃይሎችን ማፍራት መሆኑንም አምባሳደሩ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት የቀጣናው ብሎም የሁሉም አካላት ሰላም በመሆኑ ለመልሶ ማቋቋሙ ስኬት ከመንግስት ጥረት ባሻገር የሌሎች አጋር አካላት ሚና ድርሻ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ በመንግስት ብቻ የሚከናወን አይደለም ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የመገናኛ ብዙሃን የሲቪክ ማህበራት፣ ህዝቡና አጋር አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።


 

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ምክትል ሥራ አስፈፃሚ ታምራት ኃይሉ፤ የመልሶ ማቋቋም ስራው ስኬታማ እንዲሆን ሚዲያዎች የድርሻቸውን አበርክቶ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም