ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳንን የመሰረተ-ልማትና የንግድ ትስስር በማጠናከር የአገራቱን ሕዝቦች ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል- በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር

አዲስ አበባ ሀምሌ 12/2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳንን የመሰረተ-ልማትና የንግድ ትስስር በማጠናከር የአገራቱን ሕዝቦች ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ፒ ሞርጋን ተናገሩ።

የሁለቱ አገሮች የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና የዲፕሎማሲ የትብብር ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ተመስርቶ በጥሩ ሂደት ላይ ነው፤ በንግድና የመሰረተ-ልማት ትስስርም በጋራ እየሰሩ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳንን የዲፕሎማሲ ግንኙነት በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ጀምስ ፒ ሞርጋን፤ የሁለቱ አገሮች ሁለንተናዊ ትብብር በተጠናከረ መልኩ መቀጠሉን ገልፀዋል።

በወንድማማችና እህትማማችነት ላይ የተመሰረተው የሁለቱ አገራት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትም እንዲሁ።

ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ሰፊ ድንበር የሚዋሰኑ በመሆኑ ቀጣናዊ ትስሰር፣ የሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር አመቺ ሁኔታ የፈጠረላቸው መሆኑንም አምባሳደሩ ተናግረዋል።

አፍሪካን በመንገድ፣ በባቡር፣ በኃይልና ሌሎችም መሰረተ-ልማቶች በማስተሳሰር አህጉራዊ እድገት የማምጣት ዕቅድ መያዙን ጠቅሰው፤ በዚሁ ዙሪያ ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን በጋራ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል። 

በቅርቡ የሁለቱን አገራት ዋና ከተሞች የሚያገናኝ መንገድ ለመገንባትም የሁለቱ አገሮች የገንዘብ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ስምምነት መፈራረማቸውን ጠቅሰዋል።

የመንገዱ ግንባታ ሲጠናቀቅም የንግድ ልውውጥን በማሳደግና የተፈጥሮ ኃብትን በጋራ አልምቶ በመጠቀም የጋራ እድገትን ለማምጣት የላቀ አስተዋጽዖ አለው ብለዋል።

ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት መቻሏ አህጉሪቱን በኃይል አቅርቦት ለማስተሳሰር እየተከናወነ ያለውን ተግባር የሚያጠናክር ስለመሆኑም አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያም ከደቡብ ሱዳን የነዳጅ አቅርቦት እያገኘች በመሆኑ የአገራቱ የጋራ ተጠቃሚነት በተጠናከረ መልኩ  ይቀጥላል ነው ያሉት።

ከጦርነትና የእርስ በርስ ግጭት ነፃ የሆነች አፍሪካን እውን በማድረግ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የጋራ ትብብር ወሳኝ መሆኑን አምባሳደሩ ጠቁመዋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና አፍሪካውያንን ወደ አንድነት በማምጣት ለድህነት ቅነሳ የላቀ ፋይዳ የሚኖረው መሆኑንም ገልፀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም