በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ ያስመዘገብነውን ስኬት በሌሎች የልማት ሥራዎች መድገም እንደሚቻል ተገንዝበናል- አስተያየት ሰጪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ ያስመዘገብነውን ስኬት በሌሎች የልማት ሥራዎች መድገም እንደሚቻል ተገንዝበናል- አስተያየት ሰጪዎች
አርባ ምንጭ፤ ሐምሌ 12 ቀን 2015 (ኢዜአ) ፡- በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ያስመዘገቡትን ስኬት አንድነታቸውን በማጠናከር በሌሎች የልማት ሥራዎችም መድገም እንደሚቻል መገንዘባቸውን በጋሞ ዞን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አመራሮችና ነዋሪዎች ተናገሩ።
የጋሞ ዞን ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ መልካሙ ቶንቼ ፣ በአንድነት በመውጣት ሀገራዊ የአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላው መርሃ ግብርን ለማሳካት በአካባቢያቸው በመሳተፍ የድርሻቸውን መወጣታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው ቀኑን ሙሉ ለችግኝ ተከላው ያሳዩት ተነሳሽነትና ትጋት በቀጣይ በልማት ሥራዎች ላይ በመድገም ታሪክ መሥራት እንደሚቻል መገንዘባቸውን ተናግረዋል።
ያለመግባባት ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮች እየለየንና እያጠበብን አብሮነታችንን በማጠናከር ለዘመናት ያዳበርነውን የሰላም ዕሴት እያጠናከርን መሄድ ይገባል ሲሉም አስተያየት ሰጥተዋል።
በተለይም ያሉንን ጸጋዎች ማልማትና መጠቀም ላይ የተሰጠው ትኩረት የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ለማሳደግ እያነቃቃ ይገኛል ያሉት አቶ መልካሙ ፤ ይህን በማጠናከር ከራስ አልፎ ሥራ ለመፍጠርና ገቢ ለማመንጨት ያስችላል ብለዋል።
በተቀናጀ መንገድ በአንድ ጀምበር በማካሄድ የተገኘው ስኬት በአብሮነት በሁሉም ዘርፎች አስደናቂ ስኬቶች ማስመዝገብ እንደሚቻል ማሳያ ነው ያሉት የጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዓባይነህ አበራ ናቸው።
በየአካባቢው ያሉት ጸጋዎች ህዝብን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ በማስተባበር ስኬታማ ለመሆን እንደሚሰራ ያመለከቱት አቶ ዓባይነህ፤ አካባቢው ያለውን የእንስሳት ሀብትና በፍራፍሬ እምቅ አቅም ተጠቅመን እናለማለን ሲሉ ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት የተጀመረውን የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አመልክተዋል።
ለዚሁም የወረዳውን አመራርና ህዝብ በማስተባበር ልማቱን ለማረጋገጥ የመሪነት ሚናዬን እወጣለሁ ብለዋል።
የጨንቻ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ አዲስዓለም ደበበ በሰጡት አስተያየት፤ የችግኝ ተከላው መርሐ ግብር ለማሳካት ተሳትፎ በማድረግ መደገፋቸውን ገልጸዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻው አብሮነታችንና አንድነታችን ይበልጥ እንዲጎለብት ያስቻለ ነው ያሉት ወይዘሮ አዲስዓለም፤ በዚህም ድህነትን ታሪክ ማድረግ እንደሚቻል መገንዘባቸውን ተናግረዋል።
የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ መምህር አሳዬ ካሳዬ በበኩላቸው ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድ ጀምበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ያስመዘገበው ስኬት የአንድነትና የትብብር ውጤት መሆኑን አመልክተዋል።
ይህንን አጠናክሮ ማስቀጠል ከተቻለ ሰላምና ልማት የማይረጋገጥበት ምክንያት እንደማይኖር ገልጸው፤ በቀጣይም ሁሉም እጅ ለእጅ በመያያዝ በየተሰማራበት መስክ ተግቶ በመስራት ለተሻለ ውጤት የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።