ተመራቂዎች በቀሰሙት ዕውቀትና ክህሎት ለሀገራቸው እድገትና ብልፅግና የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል-አምባሳደር መሐሙድ ድሪር - ኢዜአ አማርኛ
ተመራቂዎች በቀሰሙት ዕውቀትና ክህሎት ለሀገራቸው እድገትና ብልፅግና የድርሻቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል-አምባሳደር መሐሙድ ድሪር
ድሬዳዋ ፤ ሐምሌ 12 ቀን 2015(ኢዜአ) ፡- ተመራቂዎች በቀሰሙት ዕውቀትና ክህሎት ለሀገራቸው እድገትና ብልፅግና ተግተው በመስራት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አምባሳደር ኮሚሽነር መሐሙድ ድሪር ገለጹ።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በመጀመሪያና በሁለተኛ ድግሪ መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን ከ1 ሺህ 200 በላይ ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው በዚሁ ጊዜ " ለአገርና ለህዝብ አኩሪ ስራ የሰሩ ጀግና " ብሎ ለሰየማቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷል።
በወቅቱም፤ አምባሳደር ኮሚሽነር መሐሙድ ድሪር ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት በቀሰሙት ዕውቀትና ክህሎት ለሀገራቸው እድገትና ብልፅግና ቀን ከሌት ተግተው በመስራት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝዋል።
የዕለቱ ተመራቂዎች አገራቸውን ወደ ተሻለ የዕድገት ደረጃ ለማሸጋገር በሚካሄዱ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴዎች በንቃት በመሳተፍ የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
አምባሳደር ኮሚሽነር መሐሙድ የተሰጣቸው ታላቅ ሽልማትና ክብር እንዳስደሰታቸው ገልጸው፤ ለድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ምስጋና አቅርበዋል።
አያይዘውም በቀሪ ዘመናቸው ሀገራቸውንና ህዝባቸውን ይበልጥ ለማገልገል እንደሚተጉ አረጋግጠዋል።
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ እንዳመለከተው አምባሳደር ኮሚሽነር መሐሙድ ኢትዮጵያ በራሷ ሃብት የመጠቀም ሙሉ መብቷን፤ በተለይ በህዳሴ ግድብ የመጠቀም መብቷ እንዲረጋገጥ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ ሰርተዋል።
አምባሳደር ኮሚሽነሩ በሰላም አደራዳሪነት በመሳተፍ ለአፍሪካውያን ዘላቂ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ተገቢውን ጥረት ማድረጋቸውም ተገልጿል።
በዓለም አቀፍም ሆነ በአፍሪካ የኢትዮጵያን መብት፣ ፍላጎትና ጥቅሞች የሚያስከብር ውጤታማ ግንኙነት በዲፕሎማቲክ ዘመናቸው መገንባታቸውም ተመላክቷል።
አምባሳደር ኮሚሽነሩ ኢትዮጵያ የቀደመ ስልጣኔ ታሪክ ባለቤት መሆኗን የሚያስመሰክሩ ቅርሶችን በማስመለስ ግንባር ቀደም ሚና መጫወታቸውም ተጠቁሟል።
በተጨማሪም ለኢትዮጵያ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ልማትና ዕድገት መፋጠን፤ ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ፤ ለህዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነት መጠናከርና ለዜጎች ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ያለሰለሰ ጥረት ማድረጋቸው ተገልጿል።
አምባሳደር ኮሚሽነር መሐሙድ ድሪር መስከረም 12 ቀን 1952 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ መወለዳቸውን፣ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም በዛው መከታተላቸውን ከታሪክ ማህደራቸው ለማወቅ ተችሏል።
አምባሳደር ኮሚሽነሩ ዘጠኝ የውጭ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው አንደሚናገሩ የተመላከተ ሲሆን ይህም ከሁሉም ማህበረሰብ ጋር በቀላሉ እንዲላመዱና በፍጥነት እንዲዋሃዱ እንዳስቻላቸው ተመላክቷል።
አምባሳደር ኮሚሽነር መሐሙድ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በቋንቋ፣ የሁለተኛ ደግሪያቸውን ደግሞ በዓለም አቀፍ የንግድ ትምህርት ማግኘታቸውን የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል።