በመዲናዋ በፍሳሽ ማስወገጃ ግንባታ ጥራት መጓደልና ቱቦዎች በቆሻሻ በመዘጋታቸው ለጎርፍ አደጋ እየተጋለጥን ነው- ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ በፍሳሽ ማስወገጃ ግንባታ ጥራት መጓደልና ቱቦዎች በቆሻሻ በመዘጋታቸው ለጎርፍ አደጋ እየተጋለጥን ነው- ነዋሪዎች

አዲስ አበባ ሐምሌ 12/2015(ኢዜአ) በአዲስ አበባ የመንገድ ዳር የፍሳሽ ማስወገጃ ግንባታ ጥራት መጓደልና ቱቦዎች በደረቅ ቆሻሻ በመዘጋታቸው ለጎርፍ አደጋ እየተጋለጡ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።
የከተማዋ መንገዶች ባለሥልጣን በበኩሉ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የፍሳሽ ማስወገጃ ማስተር ፕላን ጥናት ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ ነው ብሏል።
የክረምቱን ዝናብ ተከትሎ በመዲናዋ የውሃ መውረጃ ቦዮችን የፍሳሽ አወጋገድና የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነት በተመለከተ የኢዜአ ሪፖርተር በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ቅኝት በማድረግ ነዋሪዎችንም አነጋግሯል።
በቅኝቱም በአንዳንድ ቦታዎች የእግረኞች መተላለፊያም ሆነ የአስፋልት መንገዶች በውሃ ተሞልተው ለሰዎችና ለተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ፈተና መሆናቸውን ተመልክቷል።
በየካ ክፍለ ከተማ በጉርድ ሾላ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አካባቢ የሚኖሩት ወይዘሮ ነሲባ ነጋሽ እና አቶ ፍቃዱ ገላና፤ በዝናብ ወቅት አካባቢው ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ መሆኑንና ለእንቅስቃሴም አስቸጋሪ ሆኖብናል ሲሉ ተናግረዋል።
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እሳት አደጋ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የእንጨት ሥራ ላይ የተሰማራው ዮናስ እንኳንሆነ በዝናብ ወቅት አካባቢው ላይ ተንቀሳቅሶ መስራት አስቸጋሪ መሆኑን ተናግሯል።
የችግሩ አሳሳቢነት ለዓመታት የዘለቀና እስካሁንም መፍትሄ ያላገኘ መሆኑን ጠቅሶ የሚመለከተው አካል በዘላቂነት እልባት እንዲያበጅለት ጠይቋል።
በአካባቢው አሽከርካሪዎችም ሆኑ እግረኞች ለመንቀሳቀስ የሚቸገሩ መሆኑንና አንዳንዶች ጉዳትም እየገጠማቸው መሆኑን የሚናገሩት ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ አቶ ወንዱ ተፈራ ናቸው።
የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን የመንገድ ኃብት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ደሳለኝ ተረፈ፤ ክረምቱ ከመግባቱ በፊት የጎርፍ አደጋን ለመከላከል የፍሳሽ መስመር ጥገና ሥራ በስፋት ተከናውኗል ብለዋል።
በተለይም ለጎርፍ ተጋላጭ ተብለው በተለዩ 91 አካባቢዎች ላይ የግንባታ፣ ጥገና፣ የጎርፍ መከላከያ እና የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ጽዳት መከናወኑን አብራርተዋል።
የከተማዋን የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነት ለመከላከልና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የፍሳሽ ማስወገጃ ማስተር ፕላን ጥናት ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በከተማዋ የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል በተለይም የኅብረተሰቡ ደረቅ ቆሻሻን በአግባቡ የማስወገድ ግንዛቤ ለማሳደግ በቀጣይነት የሚሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ የተጀመሩ የወንዝ ዳር ፕሮጀክቶችን በማጠናከር አካባቢውን ውብና አረንጓዴ የማድረግና የጎርፍ አደጋን ለመከላከል የሚሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።