የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ስራችን አለም አቀፍ ተቀባይነትን እያገኘ ነው-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ስራችን አለም አቀፍ ተቀባይነትን እያገኘ ነው-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ሐምሌ 12/2015(ኢዜአ):-የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዲፕሎማሲ ስራ አለም አቀፍ ተቀባይነትን እያገኘ መምጣቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም በውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሳምንታዊ መግለጫ ሰተዋል።
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው በአረንጓዴ አሻራ በአንድ ጀምበር ከ566 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል በአገር አቀፍ ደረጃ ታሪክ ተሰርቷል ብለዋል።
በዚህ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልጸው በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖችም በያሉበት በዚህ ተግባር ላይ መሳተፋቸውን አስታውሰዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለዓለም አርአያ የሚሆን ነው ያሉት አምባሳደር መለስ ዓለም የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ስራ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን ገልጸዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ከኢትዮጵያ አልፎ አሁን ላይ የአፍሪካ ፕሮግራም ሆኗል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያን አረንጓዴ ታሪክ የመጻፍና የማስቀመጥ ስራ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የበኩሉን ኃላፊነት ይወጣል ብለዋል።
ሚኒስቴሩ በዚህ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ለተሳተፉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ምስጋናውን አቅርቧል።
የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈፃሚዎች 43ኛ ጉባኤ በኬንያ መካሄዱን የጠቀሱት ቃል አቀባዩ፤ የኢትዮጵያ ተሳትፎና የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ በሰፊው መካሄዱን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በሰላማዊ ንግግር ግጭቶችን በመፍታት ወደ ሰላምና መረጋጋት መግባቷም በጉባኤው በጥሩ ተሞክሮነት መነሳቱን አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ የግጭት ማስወገድ ጥረት፣የመልሶ ግንባታ፣ የሽግግር ፍትህ እና የአገራዊ ምክክር ሂደት ለመላ አፍሪካ በመልካም ማሳያነት ተነስቷል ብለዋል።