የአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በአቪዬሽን ዘርፍ ከቦይንግ ኩባንያ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን አጋርነት መሠረተ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በአቪዬሽን ዘርፍ ከቦይንግ ኩባንያ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን አጋርነት መሠረተ
አዲስ አበባ ሐምሌ 11/2015 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በአቪዬሽን ዘርፍ ከቦይንግ ኩባንያ ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችለውን አጋርነት መስርቷል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ከዩኒቨርሲቲው ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች ለኢትዮጵያ አየር መንገድ እድገት መሰረት መሆናቸውን ገልፀዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከቦይንግ ኩባንያ ጋር የጀመረው አጋርነት በአፍሪካ ያለው የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ በመላው ዓለም ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማስቻል የሚረዳ ብቁ ባለሙያ ለማፍራት እንደሚያስችል ተናግረዋል።
የቦይንግ ኩባንያ በሚያደርገው ድጋፍ የሚገነባው የንፋስ ዋሻ የሙከራ መለማመጃ ተማሪዎች በምድር ላይ የሚገጠሙ የተለያዩ ዲዛይኖችንና ሞዴሎችን ለማወቅ ይረዳቸዋል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቢቂላ ተክሉ፤ በቦይንግ ኩባንያና በኢንስቲትዩቱ መካከል የተመሠረተው አጋርነት በአቪዬሽንና በ 'ኤሮስፔስ' ኢንዱስትሪው የአቅም ግንባታ ስራ ለማከናወን የሚያስችላቸው ነው ብለዋል።
የተደረገው ድጋፍ ተማሪዎች የፈጠራ ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበት፣ የአቪዬሽንና 'ኤሮስፔስ' የምርምር ላቦራቶሪ አቅም የሚገነባበት መሆኑን ገልጸዋል።
በዕለቱ የዘርፉን የቦይንግና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁናዊ ሁኔታ የሚያስረዳ የፓናል ውይይት ተደርጓል፡፡
በፓናል ውይይቱ ላይ የቦይንግ መካከለኛው ምስራቅ፣ ተርኪዬ እና አፍሪካ ፕሬዝዳንት ኩልጂት ጋታ-ኦራ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው የተቋማቸውን መነሻ እና አሁናዊ ሁኔታ በተመለከተ ለተማሪዎቹ ገለጻ አድርገዋል።