ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተያዙ የዘላቂ የልማት ግቦችን እያሳካች ነው-አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

አዲስ አበባ ሐምሌ 11/2015(ኢዜአ)፦የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የፖለቲካ መድረክ የዘላቂ የልማት ግቦች ዕቅድ አፈፃፀም ላይ በኢትዮጵያ የተመዘገበውን እድገት አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተያዙ ዘላቂ የልማት ግቦች እንዲሳኩ ከአገራዊ በጀቷ ከፍተኛውን ድርሻ ለዘላቂ ልማት ግቦችና ለድህነት ተኮር ፖሊሲዎችና መርሃ ግብሮች በተለይም እንደ አየር ንብረት ላሉ ዘርፎች በመመደብ ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ልዩ ትኩረት በመስጠት ቁርጠኛ መሆኗን አመልክተዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዘላቂ ልማት ግቦች አፈፃፀም ዙሪያ በሚመክረው መድረክ አገራት በተያዘው እቅድ መሰረት ተግባራት እና ግቦችን መፈፀማቸውን ይገመገማል።

እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር 2030 የሚጠናቀቀው የዘላቂ ልማት ግቦች እቅድ በኢትዮጵያ በውሃ ፣በአካባቢ ንፅህና ዘላቂ እና ተመጣጣኝ ኃይል አቅርቦት፤ መሠረተ ልማት እንዲሁም የሥርዓተ-ፆታ እኩልነት ዘርፎች የተሰሩ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸው ተገልጿል።

የከፍተኛ ደረጃ ፖለቲካ መድረኩ ሀገራት የተቀመጡትን ግቦች አፈፃፀም ደረጃ ያቀረቡበት ፣ልምድ የሚለዋወጡበት እና እርስ በእርስ የሚማማሩበት ነው።

አምባሳደር ምስጋኑ ከዚህ መድረክ ጎን ለጎን ከዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ራስል ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም