የተመራቂ ተማሪዎችን የፈጠራ ስራዎች የሚያሳይ አውደ ርዕይ ተከፈተ - ኢዜአ አማርኛ
የተመራቂ ተማሪዎችን የፈጠራ ስራዎች የሚያሳይ አውደ ርዕይ ተከፈተ
አዲስ አበባ ሐምሌ 11/2015(ኢዜአ) የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የተመራቂ ተማሪዎች የፈጠራ ስራዎች የሚታዩበት አውደ ርዕይ ዛሬ ተከፍቷል።
አውድ ርዕዩ የተዘጋጀው ለሶስተኛ ጊዜ ነው።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ደረጄ እንግዳ በአውደ ርዕዩ ላይ የፈጠራ ውጤቶቻቸውን በማቅረብ የተሳተፉ የፈጠራ ባለቤቶች ከተቋማት ጋር እንዲገናኙ ይደረጋል ብለዋል።
በቴክኖሎጂው ዘርፍ ብቁና የሰለጠነ የሰው ኃይል ከማፍራት ባለፈ የፈጠራ ውጤቶች እንዲበራከቱ ዩኒቨርሲቲው እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት በተከናወኑት ሁለት አውደ ርዕዮች ከ50 በላይ ተቋማት ጋር ተመራቂ ተማሪዎችን በማገናኘት ለ43ቱ የስራ እድል መፈጠሩን ነው ያስታወሱት።
የአምስተኛ ዓመት የኢንጅነሪግ ተማሪዎቹ ኤልሻዳይ ቢኖረው እና ሚኪያስ በላይ፤ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሕብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ማበልጸግ መቻላቸውን ገልጸዋል።
በቴክኖሎጂ ዘርፍ ኢትዮጵያን ከበለጸጉ አገራት ተርታ ለማሰለፍ እያደረጉ ያለው ጥረት ፍሬ ማፍራት መጀመሩንም አመልክተዋል።
በቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚሰሩ ስራዎች ውጤታማና ጊዜ ቆጣቢ በመሆናቸው ለሕዝብ የሚጠቅሙ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን ይዘን ቀርበናል ያለችው ደግሞ ተማሪ ማህሌት ፍቅረ ነች፡፡
ያበለጸገችው የፈጠራ ውጤት ፍራፍሬዎች ሳይበላሹ ለረዥም ጊዜ ለማቆየት የሚያስችል አዲስ የፈጠራ ውጤት መሆኑን ገልጻለች።
አውደ ርዕዩ እስከ ሐምሌ 13/2015 ይቆያል።