የጤና መድህን አገልግሎትን በ2023 ዓ.ም በመላው ኢትዮጵያ ተደራሽ ለማድረግ ታቅዷል - ኢዜአ አማርኛ
የጤና መድህን አገልግሎትን በ2023 ዓ.ም በመላው ኢትዮጵያ ተደራሽ ለማድረግ ታቅዷል
አዲስ አበባ ሐምሌ 11/2015(ኢዜአ)፦ የጤና መድህን አገልግሎትን በ2023 ዓ.ም በመላው ኢትዮጵያ ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ የጤና መድህን አገልግሎት "የጤና መድህን ከየት ተነስቶ የት ደረሰ?" በሚል ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል፡፡
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ፍሬህይወት አበበ፤ ማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተግባራዊ ከተደረገ አሥር ዓመታት ማስቆጠሩን ገልፀዋል።
በ13 ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ ተጀምሮ አሁን ላይ በ1 ሺህ 6 ወረዳዎች በመተግበር ላይ ይገኛል ብለዋል።
አሠራሩን ዲጂታላይዝ የማድረግና የመዋጮ አሰባሰብን የማዘመን ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በመንግሥት የሚደረገው ድጎማም ከ10 በመቶ ወደ 25 በመቶ ማደጉን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም በ2023 ዓ.ም የጤና መድህን አገልግሎትን በመላው ኢትዮጵያ ተደራሽ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ነው ዋና ዳይሬክተሯ የገለጹት።
በውይይቱ የተሳተፉት የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ትዕግስት ተፈሪ፤ በክልሉ የጤና መድህን አገልግሎት አሰጣጥና የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በ2011 ዓ.ም 32 በመቶ የነበረውን የገቢ አሰባሰብ በአሁኑ ወቅት 89 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃብት አሰባሰብ እና ፓርትነርሽፕ አስተባባሪ አዲሱ አበባው፤ በክልሉ 96 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ ሁሉንም ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ 1 ሺህ 6 ወረዳዎችን በጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ 56 ሚሊዮን ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።