ቀጥታ፡

በዘንድሮው መኸር 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታገጠም እርሻ እየለማ ነው- የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ ሐምሌ 11/2015 (ኢዜአ) በዘንድሮው የመኸር ወቅት 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታገጠም እርሻ እየለማ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የኩታገጠም (ክላስተር) አስተራረስ የእርሻ መሬታቸው በአንድ አካባቢ የሆኑ አርሶ አደሮች የግብርና ሜካናይዜሽን ተጠቅመው በጋራ በማልማት ምርታማ የሚሆኑበት አሰራር ነው።

ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ይፍሩ ታፈሰ፤ የክላስተር አስተራረስ ውጤቱ በተግባር እየታየ በመምጣቱ በስፋት እየተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በየአካባቢው 30 እና ከዚያ በላይ አርሶ አደሮች በኩታገጠም በማረስ የተሻሻለ ምርጥ ዘር እና ሌሎች ግብአቶችን በመጠቀም ምርታማ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በዘንድሮው የመኸር ወቅት በ3 ነጥብ 9 ሚሊዮን አርሶ አደሮች 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታገጠም ታርሶ እየለማ መሆኑን ተናግረዋል።

ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጻር በኩታ ገጠም የሚያርሱ አርሶ አደሮች ቁጥር በ200 ሺህ ሲያድግ የመሬቱም መጠን መጨመሩን አብራርተዋል።

በመሆኑም በመኸሩ በአገር አቀፍ ደረጃ በብዛትም ይሁን በጥራት የተሻለ የግብርና ምርት የሚጠበቅ መሆኑን ዶክተር ይፍሩ ገልጸዋል።

በተለይም በሰብል ምርቶች ላይ ተግባራዊ ተደርጎ ውጤት የተገኘበትን የኩታ ገጠም አስተራረስ በአትከልትና ፍራፍሬም ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

በ2015/16 የምርት ዘመን በመኸር 17 ነጥብ 39 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማልማት 513 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም