ለተተከሉ ችግኞች ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ የጽድቀት መጠናቸውን ለማሳደግ እንሰራለን--የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለተተከሉ ችግኞች ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ የጽድቀት መጠናቸውን ለማሳደግ እንሰራለን--የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች
ባህርዳር ሐምሌ 11/2015 (ኢዜአ) በክረምት ለተከሏቸው ችግኞች ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ የችግኝ የጽድቀት መጠንን ለማሳደግ እንደሚሰሩ በባህር ዳር የችግኝ ተከላ መርሀግብር ላይ የተሳተፉ ነዋሪዎች ገለጹ።
ተሳታፊዎቹ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ዘርፈ ብዙ ጥቅም እያስገኘ በመሆኑ መላው ህዝብ ችግኝ ተክሎ መንከባከብን ባህሉ ማድረግ እንዳለበትም ተናግረዋል።
አስተያየታቸው ለኢዜአ ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ አቶ አስሜ ሞላ እንዳሉት፣ ችግኝ በመትከል አካባቢን መንከባከብ ካልተቻለ በአየር ንብረት ለውጥ እየመጣ ያለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም አስቸጋሪ ነው።
በየአመቱ እንደሀገር እየተከናወነ ያለው የአረንጓዴ አሻራ ልማት የተስተካከለ የዝናብ ስርጭት እንዲኖር፣ ለኑሮ ተስማሚ የሆነ አካባቢ ለመፍጠር፣ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግና፣ የኢኮኖሚ ጥቅም ለማግኘት ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ችግኝ ተክሎ ማሳደግ የዘውትር ተግባራችን መሆን አለበት ብለዋል።
በተለይ አሁን በክረምት የተተከሉ ችግኞች በበጋው ወቅት ውሃ በማጠጣትና በመንከባከብ የጽድቀት መጠናቸውን ማሳደግና ለፍሬ ማብቃት ከሁሉም እንደሚጠበቅ ነው ነዋሪው የገለጹት።
በአንድ ጀምበር የችግኝ መርሀ ግብር ላይ ችግኝ ለመትከል ልጃቸውን ይዘው የመጡት የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ አቶ በፍቅሩ በዛ በበኩላቸው እንዳሉት፣ የአረንጓዴ አሻራ ልማቱ በአየር ንብረት ለውጥ የሚከሰትን ድርቅ ለመቋቋም ጠቀሜታው የጎላ ነው።
የአካባቢ መራቆትና የደን መመናመን የግብርና ምርታማነት እንዲቀንስ በማድረጉ ይህን ለመለወጥና የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም የአረንጓዴ ልማትን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ለእዚህም ችግኞችን ተክሎ በመንከባከብ የተራቆቱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ ከማድረግ ባለፈ ለኑሮና ለሥራ ምቹ የሆነች አገር ለመጪው ትውልድ ማስረከብ ይገባል ብለዋል።
"የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ መርሀግብር ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ በርካታ ችግኞችን እንዲተክል መነሳሳትን ፈጥሯል" ያሉት ነዋሪው፣ በአየር ንብረት ለውጥ የሚመጣ ተጽኖን በዘላቂነት ለመቋቋም ችግኝ መትከልን ባህል አድርጎ ማስቀጠል እንደሚገባም አመልክትዋል።
ልጃቸው የነገ አገር ተረካቢ በመሆኗ በችግኝ ተከላው ከልጃቸው ጋር መሳተፋቸውን የገለጹት አቶ በፍቅሩ፣ ልጃቸው በልማቱ መሳተፏ አገሯንና ህዝቧን እንድትወድ የሚያደርግ መሆኑንም አስረድተዋል።
ከአባቷ ጋር ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራዋን ያሳረፈችው ታዳጊ ህጻን አሜን በፍቅሩ በበኩሏ ትናንት በተካሄደው የአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ መርሀግብር በመሳተፏ ደስተኛ መሆኗን ተናግራለች።
ችግኝ መትከል ድርቅን ለመከላከል ያስችላል ያለችው ታዳጊዋ፣ "በተለይ ለእኛ የነገ አገር ተረካቢ ህጻናት ንጹህ አየር አግኝተን ጤናማና አምራች ዜጋ እንድንሆን ትልቅ ጠቀሜታ አለው" ብላለች።
ይህም ማልዳ በመምጣት ከአባቷ ጋር በችግኝ ተከላ ሥራው ለመሳተፍ እንዳነሳሳት ተናግራለች።
"የአረንጓዴ ልማት አሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው ተረድቺያለሁ" ያሉት ደግሞ በባህር ዳር ከተማ የዘንዘልማ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አራጋው አበራ ናቸው።
ችግኝ መትከል አፈር በጎርፍና በነፋሰ እንዳይጠረግ ከመከላከል በላይ ወቅቱን የጠበቀ ዝናብ እንዲኖር ስለሚያደርግ ለኛ ለአርሶ አደሮች የግብርና ስራ ጥቅሙ የጎላ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም የለማ ደን ለእንስሳቶቻቸው መኖ በማግኘት ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑንና ለዱር እንስሳትም መጠለያ እየሆነ በመምጣቱ የችግኝ መትከልን ባህል አድርጎ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።